
ድሬደዋ፣ ሰኔ 26/2017(ኢዜአ) ፡- በድሬዳዋ አስተዳደር ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ያህል ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠሉን የአስተዳደሩ ገቢዎች ባለስልጣን ገለጸ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልሰላም መሐመድ በመሠረታዊ የታክስ ህጎች ላይ ለግብር ከፋዮች ለሁለት ሳምንታት የተሰጠው ስልጠና ዛሬ በተጠናቀቀበት ወቅት እንዳሉት፤ ገቢን ባለው አቅም ልክ ለመሰብሰብ ትኩረት ተሰጥቷል።
በዚህም ባለስልጣኑ በአስተዳደሩ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች የሚመነጨውን ሃብት የሚመጥን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የህዝብ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በፍጥነትና በፍትሃዊነት እንዲመለሱ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይ በለውጡ ዓመታት የሚሰበሰበው ዓመታዊ ገቢ በቢሊዮን ብር ደረጃ እየጨመረ ቢሆንም ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ያህል ገቢ እየተሰበሰበ አለመሆኑን አንስተዋል።
ችግሩን ለመፍታት የሚያግዙ የተለያዩ የአሠራር ለውጦች ከማድረግ ባለፈ ታማኝ ግብር ከፋዮችን በስፋት ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ።
ሰልጣኞቹም የዚሁ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይሄው ተግባር በአዲሱ የበጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ።
የባለስልጣኑ የግብር ከፋዮች ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ አክሊለ ታጠቅ፤ ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ያህል ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ ለህግ ተገዢ የሆኑ ግብር ከፋዮችን ማፍራት አንዱ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል ።

ዛሬ ስልጠናቸውን ያጠናቀቁት ግብር ከፋዮች በሁሉም የታክስ ህጎች ላይ መሠረታዊ ዕውቀት በማግኘታቸው በቀጣይ መብታቸውን አስከብረው ያለባቸውን ግዴታ በትክክል ለመወጣት ያስችላቸዋል ብለዋል።
ከስልጠናው ተሳታፊዎች መካከል አቶ አያሌው አለሙና አቶ ሙሉጌታ ብርሃኑ በሰጡት አስተያየት፤ በቆይታቸው ስለ ታክስ የተሻለ ዕውቀት መጨበጣቸውንና ለሁሉም ግብር ከፋይ መዳረስ ያለበት መሆኑን ተናግረዋል ።
በታማኝነት የሚከፍሉት ግብር ለራሳቸውና ለሀገር ዕድገትና ለውጥ የሚውል መሆኑን እንደሚረዱ ገልጸዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለታማኝ ግብር ከፋዮች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ላይ ይበልጥ ትኩረት ማድረግ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
በስልጠናው 64 የተለያዩ ተቋማት ግብር ከፋዮች፣ ሥራ አስኪያጆችና ከፍተኛ የሂሳብ ባለሙያዎች መሳተፋቸው ተመልክቷል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026