
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30/2017(ኢዜአ)፦ በአፍሪካ በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚደረጉ ትብብሮች እንዲሳለጡ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ትሰራለች ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
3ኛው የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በፎረሙ ላይ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር መሀመድ አሊ የሱፍ፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል፣ የአፍሪካ ሀገራት ሚኒስትሮች፣ የፈጠራ ባለሙያዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎችና የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ፎረሙ አፍሪካ ያላትን እምቅ ሀብት ወደ ተጨባጭ አቅም ለመቀየር፣ ሥራ አጥነትን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ፣ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትንና አህጉራዊ ትስስርን ማላቅ ዓላማ አድርጎ ላለፉት ሁለት ተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡

ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከዛሬ ጀምሮ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በመካሄድ ላይ ሲሆን እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ለሥራ ዕድል ፈጠራ በተሰጠው ትኩረት በአማካኝ በየዓመቱ ለ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ለሥራ ፈጠራው ምቹ ሥነ ምህዳር የመፍጠሩ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።
ከግሉ ዘርፍ፣ ከሴክተር መስሪያ ቤቶችና ከቀጣናዊ የልማት አጋሮች ጋር የተፈጠረው የትብብር አውድ መልካም ውጤቶች እንዲገኙ ምቹ ሁኔታ እየፈጠሩ ነው ብለዋል።
ዛሬ መገናኘታችን በርካታ ፋይዳዎች አሉት ያሉት ሚኒስትሯ የጋራ እጣ ፈንታችንን በጋራ እና በህብረት ለመጻፍ መነሳት እንዳለብን የሚያመላክት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ወቅቱ የሚጠይቀው አርበኝነት ጠንካራ የሥራ ባህል መገንባት በመሆኑ በትብብር መሥራት ይገባል ነው ያሉት።

በሥራ ዕድል ፈጠራ በኩል በአፍሪካ የሚደረጉ ትብብሮች እንዲሳለጡ ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት እንደምትሰራም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
በአፍሪካ በየዓመቱ 30 ሚሊዮን ወጣቶች የሥራ ገበያውን የሚቀላቀሉ መሆኑን ጠቅሰው፤ እንዲያም ሆኖ በርካታ ተመራቂ ወጣቶች አሁንም ሥራ ይፈልጋሉ ብለዋል።
ሚኒስትር ሙፈሪሃት ክህሎትና ሥራ ዕድል ፈጠራዎች አሁንም ያልተሻገርናቸው የቤት ሥራዎች ናቸው ሲሉም አንስተዋል።
ፎረሙ በይፋ ሲጀመር እንደ አህጉር በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ከ80 እስከ 125 ሚሊዮን ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ መያዙን አስታውሰው፤ ግቡ ብዙ ሥራ የሚጠይቅ ሆኖ በትብብርና በቁርጠኝነት ከተሰራ ሊሳካ የሚችል ነው ሲሉም አብራርተዋል።
በመድረኩ የግብርና እሴት ሰንሰለት፣ ዲጂታላይዜሽንና የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ በተለይ ለሴቶችና ወጣቶች ምቹና አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትስስርን ማላቅ ላይ ያተኮረ ምክክር ይደረጋል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026