
ባህር ዳር፤ ሐምሌ 17/ 2017 (ኢዜአ)፦በአማራ ክልል ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ለሚቀርቡ የሰሊጥና አኩሪ አተር ልማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ የክረምት መግባትን ተከትሎ በተሰራው ሥራ እስካሁን 500 ሺህ ሄክታር መሬት በሰሊጥና በአኩሪ አተር ሰብሎች በዘር መሸፈኑ ተመልክቷል።

በቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር ማንደፍሮ አስላከ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በክልሉ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለወጪ ንግድ የሚሆኑ ሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው።
በዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን 781 ሺህ ሄክታር መሬት በአኩሪ አተርና ሰሊጥ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ በተሰራው ስራ እስካሁን ድረስ 500 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ተችሏል ብለዋል።
ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸርም ያልታረሰ ቀሪ መሬት እንዳለ ገልጸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁሉንም መሬት በመዝራት ወደ አረምና እንክብካቤ ሥራ ለመግባት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ የምርት ማሳደጊያ ግብአትና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የአኩሪ አተርን አማካይ ምርታማነት በሄክታር ወደ 28 ኩንታል፤ ሰሊጥን ደግሞ ወደ ዘጠኝ ኩንታል ለማሳደግ ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው።
በአሁኑ ወቅት ያለው የዝናብ ስርጭት ለዘር ሥራና ለሰብል ልማቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ በመኸር እርሻ ለኢንዱስትሪዎች ግብአት እና ለውጪ ንግድ የሚሆን በቂ ምርት ለማምረት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።
በአኩሪ አተርና ሰሊጥ ከሚለማው ሰብል ከ13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ጥራቱን ጠብቆ ለማምረትና ለገበያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑንም ማንደፍሮ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ባለሃብት አቶ ሃብቱ ጽዱ በበኩላቸው እንዳሉት፣ 643 ሄክታር መሬት ገበያ ተኮር በሆኑ ሰብሎች በመሸፈን እያለሙ ይገኛሉ።በዚህም ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ሱፍ እና ጥጥ እያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የዘር ሥራቸውን አጠናቀው ወደ አረምና እንክብካቤ ሥራ መግባታቸውንና ከልማቱም የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
በዘንድሮ የመኸር ወቅት ከአምስት ሄክታር በላይ መሬት በሰሊጥና አኩሪ አተር ሰብል ማልማታቸውን የገለጹት ደግሞ በዞኑ የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደር ታደሰ አይናለም ናቸው።
የዝናብ ሥርጭቱ ለሰብል ልማቱ አመቺ ሁኔታን በመፍጠሩ የተሻለ ምርት አገኛለሁ ብለው እንዲጠብቁ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ከክልሉ ግብርና ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በ2016/2017 የምርት ዘመን በክልሉ በሰሊጥና በአኩሪ አተር ሰብል ከለማው መሬት 10 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ተሰብስቦ ለገበያ ቀርቧል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026