🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ሰኔ 18/2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተረጋጋ፣ ተገማችና ተወዳዳሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥነ ምህዳር መፍጠሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
በኢትዮጵያና እንግሊዝ መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ የተዘጋጀው የ“እንግሊዝ-ኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም 2026” በለንደን ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ ረገድ ተስፋ ሰጭ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን፣የተረጋጋ፣ ተገማችና ተወዳዳሪ የንግድና ኢንቨስትመንት ሥነ ምህዳር መፍጠር ችሏል።
ኢትዮጵያና እንግሊዝ ከረጅም ጊዜ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ባሻገር ጥልቅና ሁሉን አቀፍ የትብብር ታሪክ ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም በንግድ፣በልማት አጋርነት፣ በኢንቨስትመንት መስፋፋት እንዲሁም በማደግ ላይ ባለው የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ አማካኝነት የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወሳኝ በሆነ የኢኮኖሚ ሽግግር ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፥የዚህ ሽግግር ስኬት እውን ሊሆን የሚችለው በጠንካራና ተለዋዋጭ የሕዝብና የግል አጋርነት እንዲሁም በግሉ ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2019 የጀመረችውን የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሀምሌ 2024 ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረጓን አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲና ጠንካራ የታክስ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሪፎርም ተደርገው ቁልፍ የኢኮኖሚ ዘርፎች ለግሉ ዘርፍ ክፍት ሆነዋል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከጥቂት ዓመታት በፊት ለውጭ አልሚዎች ትልቅ ፈተና የነበረው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ችግር በሪፎርሙ አማካኝነት ሊፈታ መቻሉንም አረጋግጠዋል፡፡
ይህ ማክሮ-ኢኮኖሚያዊ ሪፎርም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭና ገንቢ ውጤቶችን ማስመዝገቡንም አብራርተዋል፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚው ሪፎርም የሀገር ውስጥ ገቢ በ61 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ጠቅሰዋል፡፡
ወደ ውጭ የሚላከው የምርት መጠን በ119 በመቶ እድገት ማስመዝገቡንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት፣ በአፍሪካ ትልቁ ገበያና እምቅ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግብርና የሀገሪቱን ጥቅል ሀገራዊ ምርት (GDP) 40 በመቶ የሚሸፍን፣ 80 በመቶ የሚሆነውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ የሚያስገኝና 75 በመቶ የሥራ ዕድል የፈጠረ የኢኮኖሚው ምሰሶ ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ባለሀብቶች በዘመናዊ ግብርና፣በግብርና ምርቶች ማቀነባበርና እሴት መጨመር ላይ በስፋት በመሰማራት ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
ሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነት ለማሳደግ፣ ለተኪ ምርቶች ትኩረት ለመስጠትና ከዓለም አቀፍ የእሴት ሰንሰለት ጋር ለመቀላቀል ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ “የኢትዮጵያ ታምርት” ንቅናቄ በስፋት እየተተገበረ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
ወርቅን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝና ስትራቴጂካዊ ማዕድናት መገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ውስጥ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ የሪፎርም ተግባራት በርካታ የውጭ ኢንቨስተሮችን እየሳቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ የንግድና ኢንቨስትመንት ሁኔታ ከበፊቱ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ጠቁመው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማስፋፋትና ተቋማትን በማጠናከር እጅግ ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ መፈጠሩን ገልጸዋል።
የሪፎርም አጀንዳው ዋነኛ ትኩረት ተቋማትን ማጠናከር እንደሆነና ይህም የዓለም የንግድ ድርጅት አባልነትን ጨምሮ ከዓለም አቀፍ ደረጃዎች ጋር የተጣጣመና የኢንቨስተሮችን መብትና ፍላጎት ማዕከል ያደረገ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የግሉን ኢንቨስትመንት እንደ ረጅም ጊዜ የልማት አጋር እንደምትመለከት የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የእንግሊዝ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩ በሯ ክፍት መሆኑን በማረጋገጥ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ሚዛን አማን፣ ሰኔ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ስራዎችን ተደራሽ የማድረግ ተግ...
Jun 25, 2026
ጂንካ፤ሰኔ 15/2018(ኢዜአ) ፡-የኃይለማርያምና ሮማን ፋውንዴሽን ከመንግሥት ተቋማት ጋር በመቀናጀት በሚያደርግላቸው ድጋፍ ተጠቃሚ መሆናቸውን በደቡብ ኦሞ እና...
Jun 23, 2026
ዱራሜ፤ ግንቦት 28/2018 (ኢዜአ) ፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በግብርና ዘርፍ ያሉ ፀጋዎችን ለልማት በማዋል የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የተጀመሩ ሥ...
Jun 6, 2026
ደሎ መና፤ ግንቦት 17/2018 (ኢዜአ)፦ የአርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያግዙ ዘመናዊ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑ...
May 26, 2026