🔇Unmute
አዲስ አበባ ፤ሐምሌ 5 /2018 (ኢዜአ)፦ባለፉት የለውጥ ዓመታት ደብረማርቆስን ጨምሮ አምስት የሀገር ውስጥ የአውሮፕላን ማረፊያዎች ተገንብተው አገልግሎት መጀመራቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው በሥነ-ሥርዓቱ ላይ፤ አየር መንገዱ ይህን ግዙፍ መሠረተ ልማት ገንብቶ ለደብረ ማርቆስ ከተማና ለአካባቢው ነዋሪዎች አስተማማኝ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረቡን ገልጸዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ለደብረ ማርቆስ ከተማ የበረራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከ50 ዓመታት በፊት ነበር።
ይሁን እንጂ አየር መንገዱ "ዲሲ-6" (DC-6) አውሮፕላኖችን ከአገልግሎት ውጭ ሲያደርግ፣ በረራው ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ መቆየቱን አስረድተዋል።

ለበረራው መቋረጥ ዋነኛው ምክንያት፣ አየር መንገዱ ለሀገር ውስጥ በረራ የመደባቸው አውሮፕላኖች ትላልቅ በመሆናቸው እና በወቅቱ የነበረው የደብረ ማርቆስ አውሮፕላን ማረፊያ እነዚያን አውሮፕላኖች ማስተናገድ አለመቻሉ እንደነበር ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት የአካባቢው ማኅበረሰብ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ ሲፈልግ፣ አድካሚውን የዓባይ ወንዝ ሸለቆ በማቋረጥ 300 ኪሎ ሜትር በመኪና መጓዝ ብቸኛ አማራጭ ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ የመንገድ ላይ ችግሮችን ለመሸሽ፣ ነዋሪዎች ወደ ባሕር ዳር በመኪና ተጉዘው በዚያ በኩል ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አንስተዋል።
የሕዝቡን የዘመናት ጥያቄ የመለሰው የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር፣ ኅብረተሰቡ ወደ አዲስ አበባ ወይም ባሕር ዳር ከአንድ ሰዓት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በደኅንነቱና በምቾቱ በተጠበቀ የአየር ትራንስፖርት እንዲጓዝ የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሙከራ በረራ ሲጀመር በሳምንት ሦስት በረራዎች ብቻ ይበቃሉ የሚል ግምት የነበረ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዓት በቀን ሦስት ወይም በሳምንት 21 በረራ መድረሱን አቶ መስፍን ገልጸዋል።

ይህ የሚያሳየው የአየር ትራንስፖርት ፍላጎት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ ነው ብለዋል።
አውሮፕላን ማረፊያው ለአካባቢው ማኅበረሰብ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ኢንቨስተሮች ወደ አካባቢው እንዲመጡና እንዲያለሙ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር፣ እንዲሁም የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች የአካባቢውን መስህቦች እንዲጎበኙ ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
የደብረ ማርቆስ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አውሮፕላን ማረፊያ 2,400 ሜትር ርዝመትና 30 ሜትር ስፋት ያለው በመሆኑ፣ በመደበኛነት "ኪው 400" (Q400) አውሮፕላኖችን፣ አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ "ቦይንግ 737" አውሮፕላኖችን ማስተናገድ ይችላል።
አውሮፕላን ማረፊያው ባለፉት ስምንት የለውጥ ዓመታት ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች አምስተኛው፣ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙት የሀገር ውስጥ አውሮፕላን ማረፊያዎች ደግሞ 25ኛው ነው።
በዚሁ የለውጥ ዘመን ግንባታቸው ከተጀመረው አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎች መካከል ሌሎቹ ሁለቱ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ ሲሆን በቅርቡ አገልግሎት እንደሚጀምሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተልዕኮዎቹ አንዱ የሀገሪቱን የአቪዬሽን መሠረተ ልማት መገንባት፣ ማስፋፋትና ማዘመን መሆኑንገልጸዋል።
ይህን ተልዕኮ ለማሳካት አየር መንገዱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ በርካታ አዳዲስ የአውሮፕላን ማረፊያዎችንና የመንገደኛ ማስተናገጃ ተርሚናሎችን በመገንባት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሸገር፣ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በሸገር ከተማ በተጠናቀቀው በጀት አመት አርሶ አደሩን በመደገፍ ምርትና ምርታማነቱን እንዲያሳድግ የተከናወኑ ተግባራት ስኬታ...
Jul 27, 2026
አምቦ፤ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ሸዋ ዞን የሰፈነው ስላም የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ እን...
Jul 24, 2026
ጎንደር፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በማእከላዊ ጎንደር ዞን የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የዞኑ ከተማ እና መሠረተ ልማት መምሪያ...
Jul 23, 2026
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 8/2018 ( አዜአ) ፦ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአፍሪ ኤክሲም ባንክ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤሎምቢ (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።...
Jul 16, 2026