ሀዋሳ፤ጥር 4/2017 (ኢዜአ)፡-መንግስት ለዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩ የፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀም ለውጤታማነቱ በቅንጅት እንደሚሰሩ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ገለጹ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ የምርምር ተቋማትና የኢንዱስትሪዎች ትስስር አዋጅ (1298/2015) ከዚህ ቀደም በተጠናጥል የሚከናወኑ ሥራዎችን በቅንጅት ለመስራት የሚያስችል ነው።
ትምህርት ሚኒስቴርም አዋጁን መሰረት በማድረግ በአገሪቱ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች በአምስት ክላስተሮች ተደራጅተው በቅንጅት እንዲንቀሳቀሱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
በደቡብ ቅርንጫፍ የተደራጁት ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎች በአዋጁና በቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ በሀዋሳ ዩኒቨርኒሲቲ መክረዋል።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዲላ፣ ጅማና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች መንግስት ለዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩ የፈጠረውን ምቹ ዕድል በመጠቀም ለውጤታማነቱ ተቀናጅተው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ፊሬንጆ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር በአዋጅ መደገፉና አገራዊ መዋቅር እንዲኖረው መደረጉ ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ነው።
ዩኒቨርሲቲው ከ20 ኢንዱስትሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር በምርምርና ስልጠና የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ዘንድሮም ከስምንት ተጨማሪ ኢንዱስትሪዎች ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ለዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር እንደአገር የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ የትምህርት ተቋማቱ በቅንጅት እንዲሰሩ እድል ከመፍጠር ባለፈ አገራዊ አበርክቷቸውን ያሳድጋል ብለዋል።
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ተፈራ መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው አዲሱ አዋጅ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩን እንደሚያጠናክር ነው የገለጹት።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በግብርና፣ ጤናና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከሚሰሩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፣ አዋጁ እነዚህን የተጀመሩ ሥራዎች ከማጠናከር ባለፈ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ እንዲሰሩ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ይርጋለም የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ከተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ታፈሰ ማቲዎስ (ዶ/ር) ናቸው።
በተፈጠው ትስስር ለኢንዱስትሪው ችግር ፈቺ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መፍጠርና የምርምር ውጤቶችን ማቅረብ እንደተቻለ ጠቁመው፣ አዋጁ ትስስሩ ህጋዊ መሰረት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው መስክ ምርታማነት የሚያሳድጉ ምርምሮችን የማድረግና አሲዳማ አፈርን የማከም ሥራ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የክልሉን የኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ ማጠናቀቁንም ተናግረዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስ...
Feb 28, 2025
ደሴ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን ገለ...
Feb 24, 2025
አሶሳ ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ):- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ የልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ ቀንድ...
Feb 12, 2025