አዲስ አበባ፤ የካቲት 3/2017(ኢዜአ)፡- የመንግሥት አገልግሎት አስተዳደር ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስትራቴጂዎችና የአሰራር መመሪያዎች ዝግጅት መጠናቀቁን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) አስታወቁ።
የተሟላ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን እውን ለማድረግ አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ጊዜው የሚጠይቀውን ዘመናዊ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የለውጥ ሥራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለውጡን ተከትሎ በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ዘርፍ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂ እና አደረጃጀት ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የአሰራር ሥርዓት እየተዘረጋ መሆኑን ገልጸው፤ የዓለም እና አህጉር አቀፍ እንዲሁም ሀገር አቀፍ ተሞክሮዎች ተዳሰው የተካተቱበት የመንግሥት አገልግሎት አስተዳደር ፖሊሲ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን ጠቅሰው፤ ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚረዱ ስትራቴጂዎች፣ የአሰራር መመሪያዎች ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
እንደ ኮሚሽነር መኩሪያ ገለጻ፤ የማስፈጸሚያ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀ ሲሆን፤ ስታንዳርድ ዝግጅትም በስፋት እየተሰራበት ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያላቸው 70 ስታንዳርዶችን ተግባራዊ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በፌዴራልና በክልሎች የሚሰሩ ሥራዎች እንዴት መናበብ ይችላሉ? አደረጃጀቱ እንዴት ውጤታማ በሆነ መልኩ ይከናወናል በሚለው ዙሪያ ጥልቅ የሆነ የለውጥ ሥራዎች በሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።
ሰራተኞች በሥራ አፈጻጸማቸው ተመዝነው የማትጊያ ማበረታቻዎች የሚያገኙበት ሥርዓት እንደሚዘረጋ ጠቁመው፤ ይህም ለሥራ ውጤታማነት መሻሻል አወንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል።
ሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ከለውጥ ሥራዎች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
የለውጥ ሥራዎቹ ግባቸውን እንዲያሳኩ ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ጠቁመው፤ አገልግሎቱን የማሻሻል ሥራው ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም ብለዋል።
የመንግሥት ሰራተኛው ከጊዜው ጋር ራሱን እያዘመነ እንዲሁም የመፈጸም አቅሙን እያሻሻለ መሄድ እንደሚጠበቅበትም ነው ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ(ዶ/ር) ያመላከቱት።
ተገልጋዮችም የሚገጥማቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለሚመለከታቸው አካላት ጥቆማ በመስጠትና በማጋለጥ የመፍትሄው አካል መሆን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስ...
Feb 28, 2025
ደሴ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን ገለ...
Feb 24, 2025
አሶሳ ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ):- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ የልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ ቀንድ...
Feb 12, 2025