ወላይታ ሶዶ፤ግንቦት 4/2017(ኢዜአ)፦የወላይታ ሶዶ ግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በመሳተፍ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውስጥ ገቢውን እያሳደገ መሆኑን አስታወቀ።
የኮሌጁ ዲን አሉላ ታፈሰ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፥ ኮሌጁ ከመማር ማስተማር ሥራ በተጨማሪ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በእንስሳትና በዶሮ ልማት ውጤታማ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ የሚያመርታቸውን ምርቶች ለማህበረሰቡ ከማቅረብ ባለፈ በዘርፉ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ተግባር እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የሥጋ ዶሮዎችን፣ እንቁላልና የወተት ምርቶችን ጨምሮ የተለያዩ አትክልቶችን በማምረት ለአካባቢው ነዋሪዎች በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ገበያ የማረጋጋት ሥራ እያከናወነ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮሌጁ የወተት ምርት ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚያቀርብ ገልጸው፣ በዚህም ለአካባቢው ማህበረሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማጠናከር ባለፈ የኮሌጁን የውስጥ ገቢ እያሳደገ ነው ብለዋል።
ኮሌጁ በሚያከናውናቸው የሌማት ትሩፋት ሥራዎች ከ100 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቋሚ እና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አሉላ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በእንስሳት እርባታ ዘርፍ ሰፋፊ ሥራዎች መጀመራቸውን የገለጹት ደግሞ በኮሌጁ የእንስሳት እርባታ ባለሙያ አቶ በረከት በቀለ፥ ህብረተሰቡ በኮሌጁ የሌማት ትሩፋት ሥራ በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ እየሆነ ነው።
ኮሌጁ ምርቶችን በዝቅተኛ ዋጋ ከማቅረብ ባለፈ በዘመናዊ የእንስሳት እርባታ ላይ የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አመልክተዋል።
ኮሌጁ ወተትና እንቁላልን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ገበያውን እያረጋጋ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ማለዳወርቅ ሉቃስ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
ህብረተሰቡ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዘላቂነት ተጠቃሚ እንዲሆን ግንዛቤውን ከማሳደግ ባለፈ የዘር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሻሼ ሻጎ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፥ ኮሌጁ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እያከናወነ ባለው ተግባር የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም በጥቃቅን የችርቻሮ ንግድ ሥራ ተሰማርቼ በማገኛት ጥቂት ገንዘብ ቤተሰብ ለማስተዳደር እቸገር ነበር ያሉት ወይዘሮ ሻሼ፣ አሁን ላይ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል በሚያገኙት ገቢ ያለስጋት ኑሯቸውን እየመሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የወላይታ ሶዶ ግብርና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ የተሻሻሉ የግብርና አሰራርና ቴክኖሎጂዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ ከማድረግ ባለፈ ሥራውን ለማስፋፋት ግብ ጥሎ እየሰራ መሆኑም ታውቋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስ...
Feb 28, 2025
ደሴ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን ገለ...
Feb 24, 2025
አሶሳ ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ):- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ የልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ ቀንድ...
Feb 12, 2025