አዲስ አበባ፤ ግንቦት 18/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንሹራንስ ገበያ መዳረሻ ለመሆን እየሠራች ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በአፍሪካ ኢንሹራንስን የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ ማድረግ አለብንም ብለዋል።
51ኛው የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፍረንስና ጠቅላላ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
ኮንፍረንሱ ''የክፍያ ሚዛንን ማስተካከል፦ የአፍሪካ የዕዳ ጫና፣ የሀገራት ዕዳ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራል? በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበር ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት፥ በርካታ ሀገራት በዕዳ ጫና መጨመርና በበጀት ሚዛን መዛነፍ ፈተና ላይ መውደቃቸውን አንስተዋል።
ይህም ለኢንሹራንስ ድርጅቶች ዋነኛ ስጋት መሆኑን ጠቅሰው፥ ከኢንቨስትመንት ምህዳር፣ ከንብረት ደህንነት፣ ከደንበኛ ፍላጎት እስከ ኢኮኖሚ መረጋጋት ያላቸው ሚና ላይ ከባድ ፈተና እንደሚፈጥር አስረድተዋል።
በመሆኑም የፈተና መቀልበሻ ዘዴዎችን የመፈተሽና በጋራ የወደፊት እጣ ፈንታን መቀየስ ይገባል ብለዋል።
የአፍሪካ ኢንሹራንስ አሁን ካለበት አውድ መሻሻልና መጠናከር አለበት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በአህጉሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶ መሆን እንደሚገባው በማንሳት የእያንዳንዱ ቤተሰብ ዋስትና፣ የብድር አንቀሳቃሽ እና የኢንቨስትመንት ስበት ቁልፍ መሳሪያ እንዲሆን መስራት የግድ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ፈተናዎችን የሚቋቋም ዘመናዊ ኢኮኖሚ እየገነባች፣ ተወዳዳሪነትን እያሳደገች፣ የግሉን ዘርፍ እያሳተፈች መሆኗንም ገልጸዋል።
ፈጠራን የሚያበረታታ፣ ንግድን የሚያሳድግና ኢንቨስትመንትን የሚስብ ዘላቂና አስተማማኝ ምህዳር እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
ለዚህ መሳካት ጠንካራ የፋይናንስ ስርዓት መኖር ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የኢንሹራንስ ዘርፉ ደግሞ የፋይናንስ ስርዓቱ መሠረት ነው ብለዋል።
ይህን በመገንዘብም መንግሥት ወሳኝ የለውጥ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፥ ጠንካራና ገለልተኛ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ተቋም መቋቋሙን ገልጸዋል።
ይህ አዲስ ተቋም ፈጠራን የሚያበረታታ፣ ውጤታማ ቁጥጥርን የሚያጠናክርና ከሁሉም በላይ ደግሞ የፖሊሲ ባለቤቶችን ከስጋት ይከላከላል ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ አዳዲስ በሮች እየከፈተች መሆኗን ጠቅሰው፥ በቅርቡ መንግሥት የማይንቀሳቀስ ንብረት አጠቃቀምና ባለቤትነትን የሚደነግግ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።
ይህም በመኖሪያ ቤት፣ በመሠረተ ልማት እና በሪል ስቴት ለአዳዲስ የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ መፍትሄዎች ትልቅ ዕድል የሚፈጥር እንደሆነም አመልክተዋል።
በመሆኑም ኢንቨስተሮች ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑን መገንዘብ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተመራጭ የኢንሹራንስ ገበያ መዳረሻ ለመሆን መዘጋጀቷን ጠቅሰው፥ ለዚህ ጉዞ መሳካት መንግሥት በሙሉ አቅም እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት የአህጉሪቱ የኢንሹራንስ አገልግሎትን ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረትም አድንቀዋል።
በኮንፍረንሱ ከአፍሪካ እና ሌሎች የዓለም ክፍሎች የመጡ 2ሺህ የሚጠጉ የኢንሹራንስ ተቆጣጣሪ ባለስልጣናት የኢንሽራንስ ኢንዱስትሪ ሃላፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ47 የአፍሪካ እና በ12 ከክፍለ አህጉሩ ውጭ ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ 400 አባላት ያሉት ሲሆን የአፍሪካን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋትና ለማሳደግ እ.ኤ.አ በ1972 የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የሀገሪቱን የኢንሹራንስ ዘርፍ ለመቆጣጠር በተሰጠው ስልጣን መሠረት የዚሁ ድርጅት አባል ነው፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ አዋጅን ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስ...
Feb 28, 2025
ደሴ፤ የካቲት 16/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ወሎ ዞን በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት የተሻለ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዓሊ መኮንን ገለ...
Feb 24, 2025
አሶሳ ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ):- የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ችግር ፈቺ ስራዎችን እንዲያከናውኑ እየተሰራ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገ...
Feb 24, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 4/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድ የልማት ትስስርና የኢኮኖሚ ውህደት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች እንደምትገኝ የአፍሪካ ቀንድ...
Feb 12, 2025