ጭሮ/ጊምቢ/መቱ፤ ጥር 30/2017(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ሶስት ዞኖች ባለፉት ስድስት ወራት ከ200 ሺህ በላይ የሚሆኑ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ መደረጉን የየዞኖቹ ስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽህፈት ቤቶች ገልጸዋል፡፡
የስራ እድሉ የተፈጠረው በክልሉ ምዕራብ ሐረርጌ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ኢሉአባቦር ዞኖች ሲሆን ወጣቶቹም በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የክህሎት ስልጠና የብድርና የማምረቻ ቦታ መሰጠቱም ተገልጿል።
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ ወይዘሮ አይናለም ጌታቸው እንዳሉት ባለፉት ስድስት ወራት ከ46 ሺህ 900 በላይ ወጣቶች በማህበራት ተደራጅተው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡
ለወጣቶቹ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ የብድር አቅርቦት በማመቻቸት ከ1 ሺህ ሄክታር በላይ የመስሪያ ቦታ ማቅረብ እንዲሁም የሙያ ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራ እና ክህሎት ጽህፈት ቤት የከተማ ስራ ዕድል ፈጠራ ቡድን መሪ አቶ ሀምቢሳ ተርፋ፤ በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ከ99 ሺህ በላይ ወጣቶችን በገጠርና በከተሞች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለወጣቶቹ ከ2 ሺህ ሄክታር በላይ የመስሪያ ቦታ መሬትና ከስምንት ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በኢሉአባቦር ዞን ባለፉት ስድት ወራት ከ58 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች የስራ ዕድል መፈጠሩን የዞኑ የስራ ዕድል ፈጠራና ሙያ ጽህፈት ቤት የዕቅድ ግምገማና ክትትል ስራ ሂደት መሪ አቶ ወንድሙ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡
የስራ እድል ከተፈጠረላችው ወጣቶች መካከል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን በጭሮ ከተማ በማህበር ተደራጅተው በዶሮ እርባታ የተሰማሩት ወጣት ሚሊኪ ያኪ እና ጓደኞቹ በተመቻቸላቸው የ500 ሺህ ብር ብድር በጀመሩት ስራ ውጤታማ በመሆኑ ብድሩን ከመመለስ አልፎ ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግሯል፡፡
የዚሁ ከተማ ወጣት ደምሴ ከተማ ከአምስት ጓደኞቹ ጋር በመደራጀት 100 ሺህ ብር ተበድረው በጀመሩት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ጥገና እና ንግድ ስራ ውጤታማ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን፤ ወጣት ዳንኤል ዱጋሳ ከጓደኞቹ ጋር በማህበር የጀመሩት የሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ውጤታማ እያደረጋቸው መምጣቱን አስረድተዋል፡፡
ከስራ እድል ተጠቃሚዎች መካከል በኢሉአባቦር ዞን ሀሉ ወረዳ በሻይ ልማት መስክ የተሰማራው ወጣት ታረቀኝ አስፋው እንዳለው የሻይ ቅጠልን ለገበያ በማቅረብ ገቢውን ለማሳደግ እየሰራ ነው፡፡
የዞኑ መንግስት ብዝሀ ኢኮኖሚን ለማስፋት ለሻይ ልማት የተሰጠው ትኩረትና ምርቱ በገበያ ተፈላጊ መሆኑ ገቢውን እንዳሳደገለት ተናግረዋል፡፡
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ተቋማቸውን ለተገልጋዮች ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ...
Feb 28, 2025
ወልቂጤ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ጋር በመሬት ምልከታ እና በኮሙኒኬሽን ሳ...
Feb 28, 2025
ጋምቤላ ፤የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ እርም...
Feb 24, 2025