
ሀዋሳ፤ የካቲት 6/2017(ኢዜአ)፦ ሀዋሳ ከተማን ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ በሀዋሳ ከተማ ለሚያስገነባው ሆቴል የመሰረት ድንጋይ አስቀምጠዋል።

አቶ ደስታ በዚህ ወቅት እንደገለጹት የሃዋሳ ከተማን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የተጀመሩ የተለያዩ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
የሆቴል ኢንቨስትመንት መስፋፋት ሃይማኖታዊና ሀገራዊ በዓላትን ጨምሮ በርካታ ሁነቶችን ለምታስተናግደው ሀዋሳ ከተማ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ እንዳለውም ገልጸዋል።
በመሆኑም ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ የጀመረው የሆቴል ግንባታ ከተማዋን ይበልጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ እንደሚያደርጋት ጠቅሰዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በከተማዋ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሁለተኛ ምዕራፍ ከሀዋሳ ሐይቅ ዳርቻ ልማት ጋር በማስተሳሰር እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ከተማዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎችን በማጠናከርና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን ለኑሮና ለመዝናናት ምቹ የማድረጉ ተግባር በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መኩሪያ መርሻዬ በበኩላቸው በከተማዋ ያለው ሰላም፣ የህዝቡ አንድነትና መሰረተ-ልማት ከተማዋን ለቱሪዝምና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ አድርጓታል ብለዋል።
ለሃገር እድገት ጉልህ አሻራ እያሳረፈ ያለው ሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በከተማዋ የጀመረው የሆቴልና ሪዞርት ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሆቴሎችና ሪዞርቶች ክላስተር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ዘውዴ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በሃገር እድገት ላይ ጉልህ ሚና ያለውን የልማት ሥራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዛሬ የግንባታ ሥራው የተጀመረው የ"ፎር ፖይንት ባይ ሸራተን ሀዋሳ ሪዞርት ሆቴል" በ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚከናወነው ግንባታ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል።
ሪዞርት ሆቴሉ በግንባታ ሂደት ለ500 ዜጎች፤ ግንባታው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት ሲገባም ደግሞ ለ350 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ብለዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልልና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የመንግስት አመራሮች፣ የህብረሰተሰብ ተወካዮችና የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል።
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለተቀመጡት ግቦች መሳካት ጉል...
Sep 4, 2026
አዳማ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ሥነ...
Aug 17, 2026
አዳማ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ ከልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የከተማዋ ግብርና ጽሕ...
Aug 11, 2026
አዲስ አበባ ፤ ሐምሌ 30/2018 (ኢዜአ) ፦በባሕር ዳር ከተማ የተከናወኑ አበረታች የልማት እንቅስቃሴዎች የብልፅግና አቅጣጫዎችን በግልጽ ያመላከቱ መሆናቸውን ...
Aug 7, 2026