አዲስ አበባ፤ መጋቢት 8/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ሙሉ ለሙሉ ለመተግበር በቁርጠኝነት እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ አስታወቁ።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አህጉራዊ የፋይናንስና ምጣኔ ሃብት የሚኒስትሮች ጉባኤ በሚኒስትሮች ደረጃ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ባስተላለፉት መልዕክት፥ አፍሪካ የኢኮኖሚ ዕድገት ሽግግር ለማድረግ በወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
በዚህም የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት መርህ የአህጉሪቱን ድንበር የለሽ ነፃ የንግድና አገልግሎት ግብይት መሻትን እውን ለማድረግ ከምኞት የዘለለ ስራ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ከዚህ አንፃር ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያ የንግድ ውህደት ወሳኝ ሚና የሚያበረክቱ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን አስታውቀዋል።
ለአብነትም የኢትዮ-ጅቡቲን የሚያስተሳስር የምድር ባቡር መስመር፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ፣ የቴሌኮምና የውሃ መሰረተ ልማት ግንባታዎች ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደት ምሳሌ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ አቅም የሚሆን ተመጣጣኝ፣ ታዳሽና አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።
በሌላ መልኩ ከኬኒያና ደቡብ ሱዳን ጋር የሚያስተሳስር የንግድና ትራንስፖርት መንገድ መሰረተ ልማት ግንባታም ለአህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ትግበራ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርክና ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ስራዎችም ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ ያላትን ዝግጁነት የሚያመላክቱ መሆናቸውን በማሳያነት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ፤ በአጀንዳ 2063 የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ አባል ሀገራት የገቡትን ቃል መፈጸም ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍ መሰረት የሀገራትን የመሰረተ ልማት ትስስርና አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ሥርዓት አቅሞችን ለማጎልበት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ዋና ጸኃፊ ዋምኬሌ ሜኔ፤ ብዝኅ የገበያ ሥርዓትን በማስፋት የአፍሪካውያንን የኢኮኖሚ ውህደት የሚያሳልጡ የአሰራር ሥርዓቶች እየተዘረጉ ነው ብለዋል።
አህጉራዊ የወጪና ገቢ ምርት የኤሌክትሮኒክስ ታሪፍ መጽሐ
ፍ፣ የፓን አፍሪካን የክፍያና የሸቀጥ ማስተላለፊያ ዋስትና ሥርዓቶች ስራ ላይ እንዲውሉ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም አባል ሀገራት የስምምነቱን አተገባበር መብትና ግዴታ በማስገንዘብ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን የሚፈጥር 10 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ስራ ላይ ለማዋል እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ፤ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የንግድ ሥርዓትን በማዘመን የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ጉልህ ፋይዳ አለው ብለዋል።
የዚምባቡዌ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ልማትና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ዋና ጸኃፊ እና ተሰናባቹ የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚና ልማት ሚኒስትሮች ቢሮ ሊቀመንበር አንድሪው ቡቩምቤ፤ ለአህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ያሳየነውን ቁርጠኝነት ወደ ተጨባጭ የፖሊሲ እርምጃ መቀየር ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤ አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ተቋማቸውን ለተገልጋዮች ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ...
Feb 28, 2025
ወልቂጤ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ጋር በመሬት ምልከታ እና በኮሙኒኬሽን ሳ...
Feb 28, 2025
ጋምቤላ ፤የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ እርም...
Feb 24, 2025