አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 15/2017(ኢዜአ)፦ በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው መነሻነት ባለፉት ዘጠኝ ወራት በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስ የ250 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ድጎማ መደረጉን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) አስታወቁ።
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል በሁሉም መስክ ተቋማዊ የማስፈጸም አቅምን በማጎልበት በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳስቧል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር እንዲሁም ተጠሪ ተቋማትን የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ገምግሟል።
በዚህም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ግምገማ ተደርጎባቸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ተቋማዊ የማስፈጸም አቅም፣ የሃብት አጠቃቀምና የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም የቁልፍ ውጤት አመላካች የዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቶችን አቅርበዋል።
በሪፖርታቸውም በሰው ሃብት ልማት፣ በልማት ዕቅድና በመንግስት ኢንቨስትመንት፣ በተቀናጀ የቤተሰብ ጥናት፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ የመገንባት እና ተያያዥ የዕቅድ አፈፃፀምን አመላክተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አስተማማኝ ኢኮኖሚ በመገንባት ሂደት ስኬታማ የሆኑ የልማት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በፖሊሲና ስትራቴጂ ማዕቀፍ የማሻሻልና ዝግጅት ስራም የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና የሚኖረው የካርቦን ንግድ ፖሊሲ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሕግ ማዕቀፉ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም በፓሪሱ ስምምነት አንቀጽ-6 መሰረት በቅርቡ በኮፕ-29 በአዘርባጃን ባኩ በተደረገው ስብሰባ መነሻነት ኢትዮጵያን በካርቦን ንግድ ተጠቃሚ እንድትሆን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አስቴር ከፍታው÷ በአባላቱ ምላሽና ማብራሪያ ይሻሉ ያሏቸውን ጥያቄና አስተያየቶች በጽሁፍ አቅርበዋል።
በዚህም ዓመታዊ የማክሮና የዘርፍ ልማት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት በማስመልከት በዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ መስክ የተመዘገቡ ውጤቶችን ማብራሪያ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በመንግስትና በግሉ ዘርፍ የተፈጠረው ቅንጅት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን በውጤታማነት ለመተግበር ትልቅ ዕድል እንደሰጠ አስረድተዋል።
ማሻሻያው የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን በማረጋገጥ፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከባቢን፣ የዘርፎችን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ማሻሻል እንዲሁም የመንግስትን የመፈጸም አቅም ማሻሻል የሚሉትን ወሳኝ ምሰሶዎች መያዙን አስረድተዋል።
በዚህም በዘጠኝ ወራት ውስጥ በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የተመዘገቡት ስኬቶች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የታቀደለትን ከ8 ነጥብ 4 በመቶ በላይ ማሳካት እንደሚችል አመላካች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በዕዳ አስተዳደር ሥርዓትም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ገቢያቸውን ወደ 1 ነጥብ 5 ትርሊየን ብር በማሳደግ ትርፋማ ማድረግ አንደተቻለ ገልጸዋል።
በሌላ መልኩ በዘመናዊ የገንዘብ ፖሊሲ፣ በውጭ ምንዛሬ አስተዳደር፣ በወጪ ንግድ፣ በመጠባበቂያ ገንዘብ ክምችትና የዕዳ ሽግሽግ ስኬት ማስመዝገብ መቻሉን አብራርተዋል።
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ተጋላጭነት ለመቀነስም የነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ ዘይት፣ ደመወዝና መድኃኒት ላይ የ400 ቢሊየን ብር ድጎማ ለማድረግ በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ በዘጠኝ ወራት ብቻ 250 ቢሊየን ብር የሚጠጋ መፈጸሙን አስታውቀዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ መነሻነት ተቋማዊ ማስፈጸም አቅምን በመገንባት በሁሉም መስክ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ ተቋማቸውን ለተገልጋዮች ምቹ ሊያደርጉ እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድ...
Feb 28, 2025
ወልቂጤ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህብረተሰቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦ የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን ጋር በመሬት ምልከታ እና በኮሙኒኬሽን ሳ...
Feb 28, 2025
ጋምቤላ ፤የካቲት 17/2017 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል ባለፉት ዓመታት ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ እርም...
Feb 24, 2025