
ባህርዳር፤ ግንቦት 23/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በመምህራንና ተማሪዎች የሚከናወኑ የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት ልማት ላይ እንዲውሉ እየተመቻቸ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።
"ፈጠራ ለሁለንተናዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ሃሳብ ትምህርት ቢሮው ያዘጋጀው የተማሪዎችና የመምህራን ክልላዊ የሳይንስ ፈጠራ ስራዎች አውደ ርዕይ ዛሬ ተመርቆ ለዕይታ ቀርቧል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮው ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ(ዶ/ር) እንዳሉት፤ የሀገራት ዕድገት የሚለካው በፈጠራና በቴክኖሎጂ ባላቸው አቅም ነው።
የግብርና፣ የጤና፣ የማዕድን፣ የኢንዱስትሪ እና ሌሎች ልማቶችን በአዳዲስ ፈጠራና ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ዕድገትን ለማፋጠን ከታች ጀምሮ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም የሚከናወኑ የፈጠራ ስራዎች ችግር ፈቺና የማሕበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በመፈተሽ ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

የመማርና ማስተማር ስራውም በፈጠራና ቴክኖሎጂ ማላመድ ላይ ያተኮረ እንዲሆን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም የመምህራንና የተማሪዎች ድርሻ ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
የመምህራንና የተማሪዎች የፈጠራ ስራዎችን በማበረታታት ልማት ላይ እንዲውሉ እየተመቻቸ እንደሆነም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊ የቻለ ይግዛው በበኩላቸው፤ ልማትን ለማፋጠንና የሕብረተሰቡን አኗኗር ለማዘመን አዳዲስ የፈጠራ ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።
ለዚህም ተማሪዎችና መምህራን በፈጠራ ያገኟቸውን ስራዎች ለልማት እንዲውሉ መደገፍና ማበረታታት እንደሚገባ አመልክተዋል።
በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ወደ ተግባር ተቀይረው ጥቅም ላይ እንዲውሉ ቢሮው አስፈላጊውን ቴክኒካል ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በአውደ ርዕዩ የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ሊዲያ ባዬ፤ ከአራት ጓደኞቿ ጋር በመሆን አየርን በማመቅ ውሃን ያለነዳጅ ገፍቶ በማውጣት ለመስኖ ልማት የሚያውል ቴክኖሎጂ መፍጠራቸውን አስታውቃለች።
ቴክኖሎጂው የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው በመጨመሩ ምክንያት የሚገጥመውን ችግር በመቋቋም አርሶ አደሮች በቀላል ወጪ የመስኖ ልማትን ማቀላጠፍ የሚያስችል መሆኑን አስረድታለች።
ከግንቦት 22 እስከ 25/2017 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ለዕይታ በሚቆየው አውደ ርዕይ በተማሪዎችና በመምህራን የተዘጋጁ ከ100 በላየ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች መቅረባቸውም ታውቋል።
አዲስ አበባ፤ መስከረም 1/2019 (ኢዜአ)፦የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከኃይል ማመንጫነት በላይ ትርጉም ያለው፣ የአፍሪካን የውስጥ...
Sep 14, 2026
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 28/2018 (ኢዜአ)፦በአፍሪካ ቀንድ ቀጣናዊ ውህደትን ማፋጠን ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ትግበራ እና ለተቀመጡት ግቦች መሳካት ጉል...
Sep 4, 2026
አዳማ፤ ነሐሴ 10/2018 (ኢዜአ)፡- ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ከብክነት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባና የድሬዳዋ አስተዳደር ሥነ...
Aug 17, 2026
አዳማ፤ ነሐሴ 4/2018 (ኢዜአ)፡-በአዳማ ከተማ ከልማት ሥራዎች ጎን ለጎን ከ25 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆን መሬት ታርሶ በዘር መሸፈኑን የከተማዋ ግብርና ጽሕ...
Aug 11, 2026