🔇Unmute
ሮቤ፤ ጥቅምት 25/2018(ኢዜአ)፡- መደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማከናወን አርሶ አደሩን ከተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ጋር እያስተዋወቀ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎችን ያሳተፈ የምርምር ማዕከላት የመስክ ምልከታን ዛሬ አካሄዷል።
በመስክ ምልከታው ላይ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ተባባሪ ፕሮፌሰር በዛብህ ወንድሙ እንዳሉት ፤ ተቋሙ የአርሶ አደሩን ችግር ማዕከል ያደረጉ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ ነው።
የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻልና በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በምርምር ለመለየት ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በአርሶ አደሩ አቅራቢያ የምርምር ጣቢያዎችን በመክፈት አርሶ አደሩን ከተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ጋር የማስተዋወቅ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት 200 ሺህ ሄክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ በኩታ ገጠም አስተራረስ ለተደራጁ አርሶ አደሮች ዝርያን በማላመድ፣ በአረም ቁጥጥርና በሌሎች ተዛማጅ ተግባራት ዙሪያ ሰፊ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በተጨማሪም ለአርሶ አደሩ የምርጥ ዘር አቅርቦትና ሌሎች የግብርና ድጋፎችን ከማድረግ በተጓዳኝ በእፅዋት በሽታ ቁጥጥርና ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ተግባር ተኮር ሥልጠናና ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም አንስተዋል።
አርሶ አደሩንና የዘርፉ ባለሙያዎችን ያገናኘው የመስክ ምልከታ የዚሁ ጥረት ማሳያ ነው ብለዋል።
ከምሥራቅ ባሌ ዞን የመጡት አርሶ አደር ዘውዴ ጉታ፤ በስንዴ ሰብል ልማት የመሳተፍ የረጅም ዓመት ልምድ ቢኖራቸውም በምርጥ ዘር አጠቃቀም ልምድ ማነስ ምክንያት በሄክታር ከ20 ኩንታል ያልበለጠ ስንዴ ሲያመርቱ መቆየታቸውን አስታውሰዋል ።
ከሦስት ዓመታት ወዲህ ግን በዩኒቨርሲቲው ድጋፍ ያገኙትን የስንዴ ምርጥ ዘር መጠቀም በመጀመራቸው በአንድ ሄክታር እስከ 70 ኩንታል ስንዴ ማምረት መጀመራቸውን አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተወሰነ መሬት ላይ እያከናወነ ከሚገኘው የስንዴ፣ የባቄላ፣ የጤፍና የሌሎች የሰብል ዝርያዎች ብዜት ብዙ ልምድ መቅሰማቸውን የገለጹት ደግሞ ከምዕራብ አርሲ ዞን የመጡት ከማል አልይ ናቸው።
የባሌ ዞን ጎባ ወረዳ አርሶ አደር አሚኖ አማን በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በተለያየ ጊዜ ምርጥ ዘርና ሌሎች ድጋፎችን አድርጎልናል ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው በሚያደርግልን ድጋፍም ምርትና ምርታማነታችንን እያሻሻልን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።
በመስክ ምልከታው ላይ ከባሌ ዞን፣ ምሥራቅ ባሌና ምዕራብ አርሲ ዞን የተውጣጡ አርሶ አደሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
እምድብር፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ):- የቡና ጥራትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታ...
Jul 27, 2026
ዲላ፤ ሐምሌ 13/2018 (ኢዜአ)፦ በጌዴኦ ዞን በ2018/19 የመኸር አዝመራ ወቅት ከ44 ሺህ 700 ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ታቅዶ ወደ ትግበራ መገባቱን...
Jul 21, 2026
ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚዎች በአፍሪካ የነጻነት ትግል ግንባር ቀደም በመሆን፣ የቅኝ ግዛት ቀንበርን በመስበር ለቀሪው አህጉር የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀች ሀገር ና...
Jun 27, 2026
ሮቤ፣ሰኔ 18/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል የአርሶና አርብቶ አደሩን የድርቅ ተጋላጭነት ለመቀነስ የተከናወኑ የመስኖ ልማት ሥራዎች ዜጎችን ከተረጂነት በማውጣ...
Jun 26, 2026