Feb 8, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነውን የምርጥ ዘር አቅርቦት ችግር በዘላቂነት እንደሚፈታ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጅነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ግብርናውን ለማዘመን በሰጡት ልዩ ትኩረት ተገንብቶ ለአግልግሎት የበቃው ማዕከሉ በአጠቃላይ በክልሉ የግብርና ግብዓትን በማሳለጥ እና የግብርና ቴክኖሎጂ በማቅረብ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የጎላ ፋይዳ እንዳለውም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
ከለውጡ በኃላ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ የልማት ፍትሀዊነትን ለማረጋገጥ እያደረገ ያለው የልማት እንቅስቃሴ አጅግ አበረታች መሆኑንም ገልጸዋል።
በቀጣይም ወደ ክልሉ ለሚመጡ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አና የግሉ ዘርፍ አልሚዎች ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)፣ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስረከብ የተጀመረው ስራ ውጤታማ መሆኑን ባለፉት የለውጥ ዓመታት በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ የተመዘገበው ከፍተኛ ውጤት አንዱ ማሳያ መሆኑን ነው ተናግረዋል።
በተለይም ኩታ ገጠም ግብርናን በማስፋፋት፣ የሜካናይዜሽን ተደራሽነት በማሳደግ ሁሉንም የግብርና ወቅቶች በአግባቡ ለመጠቀም የተደረገው የተቀናጀ ጥረት በአርሶ አደሩ፣ ከፊል አርብቶ አደሩ እና በዘርፉ በተሰማሩ ባለሃብቶች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትን ፈጥሯል ብለዋል።
በተጨማሪም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላለፉት የለውጥ አመታት በአማካይ ከ6% በላይ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገብ ችሏል ነው ያሉት።
ለዚህ ስኬት ታሪካዊ አሻራቸውን ካኖሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን ጠቁመው በመላ ሀገሪቱ ግብርናን የማዘመን ግብ ይዞ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡
የልማት ድርጅቱ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በገቢ እና በትርፋማነት ከሚሊየን ወደ ቢሊየን በመሸጋገር በ2016 በጀት ዓመት ከ10 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ከታክስ በፊት 1ነጥብ 8 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ትርፍ አስመዝግቧል ነው ያሉት።
ኮርፖሬሽኑ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልልን የግብርና ልማት መዳረሻ በማድረግ በካሄደው የተቀናጀ የግብርና ልማት ከክልሉ የእርሻ መሬቶችን በመረከብ ምርጥ ዘር እያባዛ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዛሬ ለምረቃ የበቃውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ ችሏል ብለዋል።
ሁለገብ ማዕከሉ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው አካባቢዎች ጭምር አገልግሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተገነባ ዘመናዊ ማዕከል መሆኑንም ገልጸዋል።
የማዕከሉ መቋቋም የምርጥ ዘር፣ የጠጣርና ፈሳሽ የአፈር ማዳበሪያዎች፣ የአግሮኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒት፣ የእርሻ መሣሪያዎች እና መለዋወጫዎች አቅርቦት በስፋት እንደሚኖር እንዲሁም የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚደረግ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የካፋ ዞንና የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ለማዕከሉ ግንባታ መሬት ከማዘጋጀት ጀምሮ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ናቸው።
ማዕከሉ ለዘርፉ መዘመንና ለምርትና ምርታማነት እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን የግብርና ግብዓቶች እና የእርሻ ተክኖሎጂ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ችሏል፤ እያቀረበም ይገኛል ብለዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ አበረታች ውጤት እያስመዘገበ በአዳዲስ ለውጦች እየመጣ መሆኑ ጠቁመው የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችለውን የISO 9001:2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓት እውቅና ማሳካት ችሏል ነው ያሉት።
በኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክት ግንባታ ታሪክ በግዙፍነቱ የመጀመሪያ የሆነውን እና 743 ሚሊየን ብር በሚጠጋ ወጪ የተገነባውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ለማስመረቅ መብቃቱን ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካለው ጠቀሜታ ባሻገር በአጎራባች ክልሎች እና ዞኖች በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ አርሶ አደሮችን፣ ከፊል አርብቶ አደሮችን፣ የልማት ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችን እንዲሁም የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም እንደዚሁ።
በአጠቃላይ ማዕከሉ የክልሉን እምቅ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ ግብርናን በማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ገልጸወል።
የማዕከሉ መከፈት ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ የሥራ ዕድል ይፈጥራል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክትል፡፡
በምረቃው ስነ-ስርዓት የግብርና ሚኒስቴር እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025