አዲስ አበባ፤የካቲት 14/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች እና የጉዞ ሰነዶች ዘመኑን የዋጁ እና የተራቀቁ የደህንነት ባህሪያት እንዲኖራቸው መደረጉ ትልቅ እመርታ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለፁ።
ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ በመጠቀም በኢትዮጵያ የተመረተ አዲስ ኢ-ፓስፖርት ዛሬ ይፋ ተደርጓል፡፡
በዚሁ ወቅት ፕሬዝደንት ታዬ አፅቀሥላሴ እንደገለፁት፥ የኢትዮጵያ ፓስፖርቶች እና የጉዞ ሰነዶች ዘመኑን የዋጁ እና የተራቀቁ የደህንነት ባህሪያት እንዲኖራቸው መደረጉ ትልቅ እመርታ ነው።
የኤሌክትሮኒክ ፓስፖርት ተግባራዊ መደረጉ የሀገርን ገጽታ ከመገንባት ባሻገር ለዜጎች የተሰጠውን ዋጋ የሚገልፅ ነው ብለዋል።
ፓስፖርቱ ማንኛውንም አይነት ማጭበርበር ለመግታት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ፕሬዝዳንት ታዬ ተናግረዋል።
ዘመናዊ ሰነዶች የሰዎችን እንቅስቃሴ ከማፋጠን ባሻገር ንግድን ለማሳለጥና ህጋዊ የስራ ዕድል ለማግኘት አስፈላጊ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ኢ-ፓስፖርቱ ለዜጎች ጥራት እና ግልፅነት የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው፥ ኢ-ፓስፖርቱ የአንድን ግለሰብ ባዮሜትሪክ መረጃ ጨምሮ የጣት አሻራዎችን፣የፊት ለይቶ ማወቂያ እና የኤሌክትሮኒክስ ቺፕስ ያካተተ እንደሆነ ገልፀዋል።
ኢ-ፓስፖርቱ የኢሚግሬሽን ሂደቶችን ማቀላጠፍን ጨምሮ ሀሰተኛ መረጃዎችን እና ማጭበርበርን ለመከላከል የሚያስችል የላቀ የደህንነት ባህሪያትን ያካተተ ነው ብለዋል።
በተጨማሪም ሀሰተኛ ፓስፖርቶችን የመስራት ወይም የሌላ ሰው ፓስፖርትን ላልተገባ ዓላማ የመጠቀም ስጋቶችን እንደሚቀንስ አረጋግጠዋል።
ከዚህም ባሻገር የኢትዮጵያን የአየርና የየብስ ድንበሮች በአግባቡ ለመቆጣጠር እና የሀገር ደህንነትን ከመጠበቅ አኳያ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አረጋግጠዋል።
ፓስፖርቱ በውስጥ ገጹ የኢትዮጵያን ቅርሶች እና ታሪካዊ ቦታዎች የሚያሳዩ ምስሎች እንዳሉትና ከዚህ ቀደም ከነበረው ፓስፖርት በቀለም እና በዲዛይን ይለያል ብለዋል።
ፓስፖርቱ በአለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ መመዘኛዎች ያሟላና አለም አቀፍ ተቀባይነትን ያረጋገጠ መሆኑ ነው የተገለጸው።
ኢ-ፖስፖርቱ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ እና በቶፓን ሴኪዩሪቲ ኢትዮጵያ አክሲዮን ማህበር አማካኝነት በሀገር ውስጥ መመረቱ በመድረኩ ላይ ተነግሯል።
በመርኃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ፣የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025