
ወልቂጤ፤ የካቲት 17/2017(ኢዜአ)፡- በወልቂጤ ከተማና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነት መሰረት ያደረጉ በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ የከተማዋ ነዋሪዎች ገለጹ።
በብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ህዝባዊ ኮንፍረንስ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

በመድረኩ የተሳተፉ የወልቂጤ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በመንግስትና በህዝብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች መልካም መሆናቸውን አንስተው ተጠናከረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ መሰረት ተሟሪ እና ወጣት ዳውድ ካሚል፤ በወልቂጤ ከተማና አካባቢው እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በጉራጌ ዞን በገጠር ኮሪደር ልማት የተሰራውን ሥራ በአርአያነት ጠቅሰው በወልቂጤ ከተማም ልማቱ በተጠናከረ መልኩ መቀጠል ይኖርበታል ነው ያሉት።
በከተማዋ የሚስተዋለው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታትም ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሙንተሃ ኢብራሂምና አቶ አቡ ገበየሁ፤ የተለያዩ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት በመንግስትና በህዝብ ትብብር እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
በጥሩ ክንውን ላይ ያሉትን በማድነቅ በተለይም የዋቤ የኤሌክትሪክ ግድብ ፕሮጀክትና የወልቂጤ ጠቅላላ ሆስፒታል ግንባታ ሥራ በአፋጣኝ ተጠናቆ ለአገልገሎት እንዲበቃ ጠይቀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ላጫ ጋሩማ፤ ህብረተሰቡ የመንግስትን ጥረት በማገዝ የልማት አጋርነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን ገልጸው በተጠናከረ መልኩ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ ይሁን አሰፋ፤ በሁሉም አካባቢዎች የልማት ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠልና ሰላምን በዘላቂነት ማስጠበቅ የጋራ አጀንዳችን ሆኖ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ፤ በየደረጃው ያለው አመራር ህዝብን በቅንነት፣ በታማኝነትና በውጤታማነት ለማገልገል ዝግጁ መሆን እንዳለበት አሳስበው የህዝቡ ትብብር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በፓርቲም ይሁን በመንግስት ደረጃ ሀገራዊ አንድነትን በማጠናከር የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት የተሟላ ዝግጁነት ስለመኖሩም አረጋግጠዋል።
የዋቤ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ሜጋ ፕሮጀክት ለመስኖ እና ለቱሪዝም ዘርፍ ጭምር አስተዋጽኦ እንዲኖረው ታሳቢ ተደርጎ እንዲለማ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ይሰራል ሲሉም አክለዋል።
የወልቂጤ ከተማን ማስተር ፕላን ለማስጠበቅ የህዝቡ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኮንፍረንሱ ከነዋሪዎች የተነሱ ሃሳቦች በቀጣይ ለተሻለ ሥራ ለመዘጋጀት አጋዥ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በህዝባዊ ኮንፍረንሱ ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራር አካላት እንዲሁም የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ተገኝተዋል።
ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Aug 27, 2026
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት...
Aug 14, 2026
ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠ...
Aug 13, 2026
ባሕር ዳር ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር...
Jul 31, 2026