ሀዋሳ፤ የካቲት 24/2017 (ኢዜአ) :- አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የጎላ ሚና እንደሚጫወት ተገለጸ።
አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲን ማስተዋወቂያ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል ፡፡
የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሃላፊ አቶ በየነ በራሳ በወቅቱ እንደገለጹት አዲሱ የግብርናና ገጠር ልማት ፖሊሲ ከዚህ በፊት ጥቅም ላይ ሲውል በቆየው ፖሊሲ ውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን የሚሞላና ያለውን የዕድገት ደረጃ የሚመጥን ነው ፡፡
ፖሊሲው የገጠሩን ክፍለ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር በማምጣት የምግብ ዋስትናና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በሲዳማ ክልል ካለው የመሬት ጥበትና ተፈጥሯዊ ሥነ-ምህዳር ጋር የሚዛመዱ የእርሻ ፣ የእንስሳት ሀብትና ሌሎች ፓኬጆች ተቀርፀው በትግበራ ላይ መሆናቸውን አውስተዋል ፡፡
ፖሊሲው ተግባራቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል ።
የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው "ፖሊሲው ከዚህ በፊት ትኩረት ተነፍጎት ለነበረው የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የወጠናቸውን የልማት ግቦች ለማሳካት ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው "ብለዋል ፡፡
ለአብነት በአሁን ወቅት በክልሉ አምስት የግል ድርጅቶች በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ ላይ ተሰማርተው 10 በመቶ የሚሆነውን የክልሉ ፍላጎት መሸፈን መቻላቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ዘርፉን በተገቢው መንገድ በማበረታታት የአርሶ አደሩን የግብዐት ችግሮች በዘለቄታው መቅረፍ እንደሚቻል ጠቅሰዋል ፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት የፖሊሲ ጥናትና የሥርዐተ ምግብ ዳይሬክተር አቶ ረታ ዋጋሪ "ላለፉት 22 ዓመታት በሥራ ላይ የቆየው ፖሊሲ የኤክስቴንሽን ሥርዐትን ከማዘመን ፣ በርካታ ባለሙያዎችን ከማፍራት እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ ውጤቶች ተገኝተውበታል" ብለዋል ፡፡
ሆኖም ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት፣ በውስጡ ያልተካተቱ ሀሳቦችን ለመጨመር እንዲሁም የዘርፉን እድገት ደረጃና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን የተመለከቱ ጉዳዮችን ለማካተት አዲሱን ፖሊሲ መቅረፅ እንዳስፈለገ ጠቅሰዋል ፡፡
ፖሊሲው በጥቅሉ በምርትና ምርታማነት፣ በአርሶ አደሩ ሕይወት፣ በሥርዐተ ምግብ፣ በምግብ ዋስትና ፣ ግብርናን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በማስተጋበር ረገድ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን ያስቀመጠ መሆኑን አመልክተዋል።
በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር)ን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል ፡፡
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025