
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 1/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል የግብርናው ዘርፍ እምቅ ጸጋዎችን ለይቶ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የአማራ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን የ10 ዓመት መነሻ ዕቅድ ላይ ከምሁራንና ከባለድርሻ አካላት ጋር በባህርዳር ምክክር ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት፤ ግብርና ለሀገር ምጣኔ ሃብትና ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ጠቅሰው፤ ገበያ ተኮር ምርቶችን በስፋት ለማምረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት የተሻሉ ውጤቶች መታየታቸውንም አንስተዋል።

ክልሉ ለግብርና ስራ ምቹ ስነ-ምህዳር ያለው እንደመሆኑ እምቅ አቅሙን ለይቶ ግብርናውን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን የበለጠ ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ ከግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የክልሉ የልማት ፍኖተ ካርታ አካል የሆነ የ10 አመት የግብርና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መዘጋጀቱን አንስተዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መሰረት የሆነው ግብርና በኋላ ቀር አሰራር ውስጥ መቆየቱ የሚፈለገው ውጤት እንዳይገኝ ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ በዘርፉ በተደረጉ የሪፎርም ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ነው የገለጹት።
የግብርና ሜካናይዜሽንና የመስኖ መሳሪያዎችን ከቀረጥ ነፃ ከማስገባት ጀምሮ አርሶና አርብቶ አደሩ በብድር የትራክተርና የኮምባይነር ባለቤት እንዲሆን ከፋይናንስ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሰራቱን አመልክተዋል።
በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ በትራክተርና በሜካናይዜሸን የሚታረሰው መሬት 5 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን ነው ያመለከቱት።
ከአፈር ማዳበሪያና ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞም ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ብቻ ከ7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት።
በዘንድሮ የምርት ዘመን ለክልሉ 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የመንግሥትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።
ክልሉ በዘርፉ ያለውን ዕምቅ አቅም ለይቶ ውጤታማ እንዲሆን መስራት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
የመነሻ ዕቅዱ ባለፉት ስድስት ወራት በግብርና ሚኒስቴር፣ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትና በክልሉ መንግሥት በጋራ ሲዘጋጅ የቆየ ነው።
ሀዋሳ፣ ነሐሴ20/2018 (ኢዜአ)፡-በሀዋሳ ከተማ የተጀመሩ የሐይቅ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Aug 27, 2026
ሐረሪ ፤ነሐሴ 7/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንቨስትመንት ፍቃድ እና መሬት ወስደው ወደ ግንባታና ማምረት ባልገቡ 12 ባለሀብቶች ላይ የኢንቨስትመንት...
Aug 14, 2026
ደሴ፤ነሐሴ 6/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ173 ሺህ ለሚበልጡ አርሶ አደሮች የሁለተኛ ደረጃ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠ...
Aug 13, 2026
ባሕር ዳር ፤ ሐምሌ 23/2018(ኢዜአ)፦በአማራ ክልል በሁሉም ዘርፎች በተከናወኑ ተግባራት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር...
Jul 31, 2026