አዲስ አበባ፤ መጋቢት 3/2017(ኢዜአ)፡- የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የአፍሪካን ጠንካራ የኢኮኖሚ ውህደት ለመፍጠር ገንቢ ሚና እንደሚጫወት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው ገለጹ።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ያዘጋጀው 57ኛው አህጉራዊ የኢኮኖሚ ልማት፣ የገንዘብና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ በባለሙያዎች ደረጃ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሰመሪታ ሰዋሰው በጉባኤው ባደረጉት ንግግር፥ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የዓለማችን ትልቁ ነፃ የንግድ ከባቢ ሲሆን፤ የጋራ የዕድገት ርዕይን እውን ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱ የአፍሪካን የኢኮኖሚ ነፃነት በማፋጠን፣ የጋራ ብልጽግናን እውን በማድረግ እና ጠንካራ ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማሳለጥ የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ለማፋጠን የጋራ ጥረት ትብብርና ቁርጠኝነት እንደሚጠይቅም አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሀገራት የመሰረተ ልማት ትስስር የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታ ኢንቨስትመንትን በማሳደግ የንግድ ፖሊሲ፣ የጉምሩክ ሂደትና የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ላይ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ በቁርጠኝነት እየሰራች እንደምትገኝ በመግለጽ።
ለአብነትም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ በመንገድ፣ በባቡር፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣናዊ ትስስርን በመፍጠር ለአሕጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ የላቀ ሚና እየተወጣች ነው ብለዋል።
በኢንዱስትሪ ፓርክና በልዩ የኢኮኖሚ ዞን ልማት ኢንቨስትመንት በመሳብ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን በማሳደግ ለአፍሪካ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር እየሰራች መሆኗንም ጠቅሰዋል።
በኃይል አቅርቦትም ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ሌሎች ውሃ ኃይል ማመንጫ ሃብቶቿ በቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ላይ የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው ብለዋል።
በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ምክትል ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ፥ የአፍሪካ ሀገራት ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነቱን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ማቀላጠፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንም ለአፍሪካውያን ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ የሚያደርገውን ያላሳለሰ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
የዚምባቡዌ የፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ልማት እና ኢንቨስትመንት ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ እና የአፍሪካ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ ልማትና ፕላን ሚኒስትሮች ቢሮ ተሰናባች ሊቀመንበር አንድሪው ብቩምቤ፤ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራ የአፍሪካውያንን እንቅስቃሴ እና የምርት ግብይት በማሳለጥ ለኢኮኖሚያዊ ውህደት ገንቢ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።
የአፍሪካ ሀገራት የነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነቱን የሚያሳልጥ የሎጂስቲክስ አቅም መገንባት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።
የባለሙያዎች ጉባዔ “የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ትግበራን ማፋጠን፤ አፈጻጸሙን የሚያልቁ ስትራቴጂካዊ እርምጃዎችን መቀየስ” በሚል መሪ ሀሳብ እስከ መጋቢት 5/2017 ዓ.ም ይቆያል።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025