አዲስ አበባ፤ መጋቢት 9/2017(ኢዜአ)፡- አፍሪካ የኢኮኖሚ እጣፋንታዋን በራሷ ለመወሰን እምቅ አቅሟን መጠቀም እንደሚገባት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ፀሐፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።
በአዲስ አባበ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን 57ኛው አህጉራዊ የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ ልማትና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ ተጠናቋል።
ዋና ፀሐፊው እንደገለጹት፤ አሁናዊ የዓለም ሁኔታ ተለዋዋጭ፣ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ አብዮት፣ የንግድና ኢንቨስትመንት ከፍ ዝቅ ማለት፣ የእርዳታ ቅነሳና የማይገመቱ ጉዳዮች ያሉበት መሆኑ በጉባኤው በስፋት ተዳሷል።
ከዚህ አኳያ አፍሪካ በዚህ ፈታኝ ወቅት የቤት ስራዋን በንቃት ከመስራት የተሻለ አማራጭ እንደሌላት መግባባት ተፈጥሯል ነው ያሉት።
ለዚህም አፍሪካ የኢኮኖሚ እጣፋንታዋን በራሷ እንድትወስን ያልተነካ ሙሉ አቋሟን አሟጣ መጠቀም እንደሚገባትና ከዚህ ቀደም ቃል የተገቡ ጉዳዮች መፈጸም እንዳለባቸው ነው ያነሱት።
በጉባኤው ቀጣናዊ ትስስርን፣ ጫናን መቋቋም የሚችል ስርዓት የንግድና ኢኮኖሚ ስርዓትን ማጠናከርን አህጉራዊ እምቅ አቅምን መጠቀም ላይ ከፍተኛ መግባባት መፈጠሩን አንስተዋል።
በጉባኤው የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ለመተግበርም በቀጣናዊ የእሴት ሰንሰለትና በሰው ሰራሽ አስተውሎት ትግበራ ላይ ሁለት የውሳኔ ሀሳቦች መጽደቃቸውን ገልጸዋል።
አፍሪካን ከሸቀጥ ጥገኝነት ለማላቀቅና የራሷን ሀብት መጠቀም እንድትችል የሚያደርግ ጠንካራ ስራ ይጠብቀናል ብለዋል ዋና ፀሐፊው።
የአፍሪካን ኢንዱስትሪ በማስፋፋት፣ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን በማጠናከርና እንዲሁም አህጉራዊ የምርት እሴት በመፍጠር የጋራ ግብን ለመፍጠር ሀገራት ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል ብለዋል።
ለዚህም በአፍሪካ በግብዓት አቅርቦት፣ በምርት ጥራትና ሰንሰለት እንዲሁም በንግድ ሂደት ላይ ያሉ አሰራሮችን መፈተሽና የተሻለ ማድረግ የግድ መሆኑን ገልጸዋል።
አፍሪካ በርካታ የኢኮኖሚ ዞኖች ያሏት መሆኗ ቀጣናዊ የእሴት ሰንለሰትን ለማጠናከርና አፍሪካን የአምራች ኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል አህጉራዊ የማህበረ ኢኮኖሚ ሽግግርን ለማሳካት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አጽንኦት ተሰጥቶታል ነው ያሉት።
ሰው ሰራሽ አስተውሎት በ2030 በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይ 1 ነጥብ 2 ትሪሊዮን ዶላር አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትና አህጉራዊ ጥቅል ምርትን በ5 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያሳድግ ጠቁመዋል።
ይህም ዘርፉ አህጉራዊ ግቦችን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንዳለው የማይካድ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑ የአፍሪካ ሀገራት በዘርፉ ላይ ስትራቴጂ ቀርጸው መንግስታዊ አገልግሎቶችን የውሳኔ አሰጣጥን ለማሻሻል እየተጠቀሙበት መሆናቸውም ትልቅ ተሞክሮ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የሰው ሰራሽ አስተውሎት ልማትን ለማፋጠን በምርምር፣ በእውቀት ሽግግርና በሌሎችም መስኮች እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት የአህጉሪቱን የንግድ ስርዓት ለማሻሻልና ተወዳዳሪ ለማድረግ ጉልህ ሚና ያለው መሆኑ ትግበራውን ለማፋጠን በሚኒስትሮች ጉባኤ መግባባት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንትንና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ለማስፋት ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ለትግበራው መፋጠን በሀገራት ደረጃ የፖሊሲ መናበብን መፍጠር እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በጉባኤው ማጠቃለያ ሞሮኮ 58ኛውን የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፋይናንስ፣ የኢኮኖሚ ልማትና የፕላን ሚኒስትሮች ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመርጣለች።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025