ቦንጋ፤ ሚያዚያ 1/2017 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የግብርና ውጤታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ውጤቶችን በማፍለቅና በማላመድ ለአርሶ አደሩ ማሸጋገሩን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ያዘጋጀው ዓመታዊ የምርምር ኮንፍረንስ እና የግምገማ መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ የግብርና ምርምር የኢንስቲትዮቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አማኑኤል ሀይሌ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ ኢኒስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሁለት የምርምር ማዕከላቱ የግብርና ውጤታማነትን የሚያሳድጉ የተለያዩ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።
በዚህም የተለያዩ የምርምር ውጤቶችን የማላመድና የማፍለቅ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለግብርና ምርታማነት ማነቆ በሆኑ ጉዳዮች፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሚያስከትለው ተጽኖ፣ በዝርያ ማሻሻል፣ በአሲዳማ አፈር ላይ እንዲሁም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ አመጣጠንና አጠቃቀም ላይ ሰፋፊ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም ገልጸዋል።
እስካሁንም ኢኒስቲትዩቱ በምርምር የተገኙ 218 የግብርና ውጤቶችን የማላመድና የማፍለቅ ሥራ መስራቱን ጠቅሰው፣ ከነዚህ ውስጥ 123ቱ ለአርሶ አደሩ መሸጋገራቸውን ተናግረዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዳይሬክተር ተመስገን ደሳለኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በዘርፉ በርካታ የምርምር ሥራዎች እንደተከናወኑና በሂደት ላይ ያሉ እንዳሉም ገልጸዋል።
የምርምር ሥራዎቹ በግብርናው ዘርፍ እየገጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በመፍታቱ ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ ፋይዳ አላቸው ብለዋል።
በተለይ በክልሉ የአፈር አሲዳማነት ጎልቶ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፣ ይህን ችግር ለመፍታት ከክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩቱ ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የዘርፉን ችግሮች ፈትቶ ውጤታማነትን ለማረጋጋጥ የተመራማሪዎች ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ተመራማሪዎች ራሳቸውን በማብቃት ለግብርና ውጤታማነት የሚያደርጉትን አስተዋፆ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ነጋ አበራ በበኩላቸው እንዳሉት፣ ክልሉ ያለውን እምቅ የግብርና አቅም ወደ ሀብትነት ለመቀየር እየተደረገ ያለው ሁሉን አቀፍ ርብርብ ዘርፉን እያነቃቃው ነው።
ከህዝብ ቁጥር መጨመር፣ ከኢንዱስትሪ ጥሬ እቃ ፍላጎት ማደግ እንዲሁም የግብርና ምርት የውጭ ምንዛሬ ምንጭ መሆኑ የግብርና ምርቶች ፍላጎትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
ይሁንና የአየር ንብረት ለውጥና የመሬት ምርታማነት መቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ላለው ጥረት ተግዳሮት መሆኑን አንስተዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በመቋቋም ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የምርምር ተቋማት ሚና የጎላ መሆኑንም አቶ ነጋ አስታውቀዋል።
የክልሉ ግብርና ኢንስቲትዩት በእንስሳት፣ በሰብል፣ በተፈጥሮ ጥበቃና በተለያዩ ዘርፎች በርካታ የምርምር ሥራዎችን መስራቱ አስታውሰው፣ ሥራዎቹ አርሶ አደሩ ማሳ ላይ ወርደው ውጤት እያመጡ በመሆኑ በቀጣይም እንዲጠናከሩ አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የምርምር ሥራዎች አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን በተጨማሪም የፎቶ ኤግዚብሽንና የመስክ ጉብኝት እንደሚካሄድ ታውቋል።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025