የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ
ግንኙነት
ፈልግ

ሀገር የምትበለጽገው በአምራች ዐርበኞች ነው-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

May 8, 2025

IDOPRESS


አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 29/2017(ኢዜአ)፦ሀገር የምትበለጽገው በአምራች ዐርበኞች ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ለአምስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው ሦስተኛው የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ተካሂዷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው፥ ኤክስፖው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን ዕምቅ ዐቅም ለማሳየት፣ የእርስ በእርስ ትሥሥር ለመፍጠር፣ ምርታቸውን ለማስተዋወቅ፣ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችን ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን ለማሰባሰብ እና የኅብረተሰቡን በሀገር ምርት የመኩራት ባህል ለማሳደግ ኤክስፖው ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ሀገር የምትበለጽገው በሁሉም መስክ የተሠማሩ ዐርበኞች ሲኖሯት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ዐርበኝነት ከራስ በላይ ሀገርን የሚጠቅም ሥራ መሥራት መሆኑንም ተናግረዋል።


አምራችነት ዐርበኝነት መሆኑን ገልጸው ኢትዮጵያ እንድትፈጥርና እንድታመርት የሚያደርጉ ዜጎች የዘመኑ ዐርበኞች ናቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግና አምራች ኢንዱስትሪው የኢኮኖሚ ሽግግር እንዲያመጣ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ወደ ተግባር መግባታቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማምረት ዐቅም አጠቃቀም በማሻሻል፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን በማሳደግ፣ ገቢ ምርትን በመተካት ትልቅ አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተዘግተው የነበሩ 837 ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን አንስተዋል።

ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ 325 ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ማምረት መጀመራቸውንም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ብሔራዊ ንቅናቄ አካል ሆኖ በየዓመቱ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ዓለም አቀፍ ኤክስፖ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን እያነቃቃ መሆኑን ተናግረዋል።

ኤክስፖው በተሳታፊ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ ለዕይታና ለገበያ በቀረቡ የምርት ዓይነቶች፣ በጎብኝዎች ብዛት፣ ከገበያ ትሥሥር አንፃር ከፍተኛ ዕድገት የታየበት ነው ብለዋል።

አምራቾች የተፈጠረላቸውን ምቹ ከባቢ በመጠቀም፣ በብዛትና በጥራት በማምረት የሀገርን ፍላጎት ለማሟላትና የወጪ ንግድ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ የሚደረገው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የለውጡ መንግሥት ማቀድ፣ መጀመር፣ በፍጥነት መጨረስ መለያው ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህንንም በአምራች ዘርፉ እንደግመዋለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ እንዲሳካላት በላቡ የሚተጋ ኢንቨስተር፣ ነጋዴ እና ባለ ኢንዱስትሪ እንደሚያስፈልጋት አንስተው፥ ሆኖም በኢኮኖሚ አሻጥር፣ የሰላም ጠንቅ በመሆን፣ በሙስና፣ በኮንትሮባንድ ሀገርን የሚበድሉ ስለመኖራቸውም ተናግረዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንድታመርት የሚተጉ ባለጸጎችን በእጅጉ ማብዛት እና የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማሳካት በህገወጥ መንገድ የተሠማሩትን ማረም እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ማምረት የህልውና አጀንዳ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሀገር አቀፍ የ2017 የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከመካሄዱ አስቀድሞ በክልሎች፣ በዞኖችና በወረዳዎች 168 የውይይት መድረኮች እና 94 የንግድ ትርኢቶች መካሄዳቸውን ገልጸው፤ በነዚህ የንግድ ትርኢቶቹ 400 ሚሊዮን ብር የሚገመት ግብይት መፈፀሙንም ጠቅሰዋል።

ማምረት የህልውና አጀንዳ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ የሀገር ውስጥ ምርትን ማስፋትና የመጠቀም ባህልን ለማሳደግ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በተከታታይ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት የ2017 ኤክስፖ በርካታ አምራቾች ምርቶቻችን እንዳቀረቡበትና ከ120 ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደተሳተፉበትም ገልጸዋል።

በኤክስፖው ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ግብይትና የገበያ ትስስር መፈጸሙን ጠቅሰው፥ የዘርፉን ማነቆዎች ለመፍታት የሚያስችሉ የፓናል ውይይቶች እንደተካሄዱም አንስተዋል።

በኤክስፖው በምርት ብዛት፣ አይነትና በመጠን ከፍተኛ እድገት ተመዝግቧል ያሉት ሚኒስትሩ፥ የሀገር የፈጠራ አቅም የታየበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ከማሸለብ ዘመን ወጥታ በዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልጸዋል።

ንቅናቄው የገጠር ኢንዱስትሪን ለመጀመር የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን በማንሳት፥ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ በመጪዎቹ ዓመታትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በቀጣይ ዓመትም ከሚያዚያ 24 እስከ 28/2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

በኤክስፖው ላይ በማምረቻው ዘርፍ የላቀ ሚና ላላቸው አልሚ በለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት - የኢትዮጵያ ድምጽ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወቅታዊ፣ ትክክለኛ እና አጠቃላይ የዜና ዘገባዎችን ለማቅረብ የሚሰራ የኢትዮጵያ የዜና ወኪል ነው። ጠቃሚ የሀገር ውስጥ እና አለምአቀፍ ሁነቶችን እንዘግባለን፣ ሀገራዊ ፖሊሲዎችን እና ማህበራዊ ለውጦችን በጥልቀት በመመርመር ለህዝብ፣ ለመንግስት ኤጀንሲዎች፣ ለንግድ ድርጅቶች እና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ታማኝ የዜና ምንጭ እናቀርባለን። ጋዜጠኞቻችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር አዳዲስ ዜናዎች እና መረጃዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲደርሱ እና ግልጽነትን እና የህዝብ ተሳትፎን ለማስተዋወቅ ነው.

መግለጫ

<p>ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው</p>

አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...

Feb 28, 2025

<p>በተሰማራንበት መስክ ውጤታማ በመሆናችን ወደ መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ማደግ ችለናል</p>

ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...

Feb 28, 2025

<p>ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው-ቋሚ ኮሚቴዎቹ</p>

አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...

Feb 12, 2025

<p>የማዕከሉ መገንባት በክልሉ የሚስተዋለውን የምርጥ ዘር ችግር በዘላቂነት ይቀርፋል - ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)</p>

አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...

Feb 8, 2025