አዲስ አበባ፤ ግንቦት 12/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉን የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በድሬዳዋ ከተማ የተገነባውን የፓዮኔር ሲሚንቶ ማኑፋክቸሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ማስፋፊያ ፕሮጀክት መርቀዋል።
በዚሁ ወቅት የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ(ኢ/ር) እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለሲሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ እንደ ለሚ ሲሚንቶ ዓይነት ግዙፍ ፋብሪካዎች ተገንብተው ስራ መጀመራቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ መሰረተ ልማት የምትገነባ ሀገር በመሆኗ የሲሚንቶ ግብዓት ወሳኝ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
አሁን ላይ የነባር ፋብሪካዎችን ምርታማነት በማሳደግና አዳዲሶችን ወደ ስራ በማስገባት ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ ለጎረቤት ሀገራት ሲሚንቶ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እየተፈጠረ ነው ብለዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት።
አራት የድንጋይ ከሰል ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ወደ ስራ በማስገባት የሲሚንቶ አምራቾችን አቅም የማሳደግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦት ምላሽ ለመስጠት በብረት፣ እብነበረድ፣ ሲሚንቶና ሌሎች መስኮች ስኬታማ የምርታማነት አቅም እየተፈጠረ መሆኑንም ሚኒስትሩ አንስተዋል።
በኢትዮጵያ እና ቻይና ባለሃብቶች አጋርነት በአጭር ጊዜ የተገነባው የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካም ከፍተኛ ጥራት ያለው ምርት በማምረት የኢትዮጵያ አዲስ የስራ ባህል ልምምድ መገለጫ ለመሆን መብቃቱን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ በማዕድን ሃብት በዓይነትም ሆነ በብዛት ከፍተኛ አቅም ያላት መሆኗን ጠቁመው፤ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ማዕድን ከድህነት መውጫ አቅም እንዲሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሀር በበኩላቸው፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ትኩረት የተሰጠው የተኪ ምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ምርታማነትንና የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ የተገነባው ፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከብክለት የጸዳ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ለስራ ዕድል ፈጠራና ለከተማዋ ኢኮኖሚ መነቃቃት ጉልህ ሚና መወጣት መጀመሩን አስረድተዋል።
የፓዮኔር ሲሚንቶ ፋብሪካ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ጄኔራል ማናጀር ሊዮን ዞን፥ ፋብሪካው ላለፉት 16 ዓመታት በኢትዮጵያ በስራ ላይ መቆየቱን አስታውሰው አሁን ላይ የማምረት አቅሙን በ600 ሺህ ቶን ማሳደጉን ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው ከሲሚንቶ ማምረት ባሻገር ማህበራዊ ሃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝም ገልጸው፤ በዚህም በድሬዳዋ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በመንገድ ስራ ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፋብሪካው አሁን ላይ ለ550 ሰራተኞች በቀጥታ የስራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን በማህበራዊ ዘርፉም የዜጎችን ተጠቃሚነት ከፍ የሚያደርጉ የስራ ዕድሎችን መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025