አዲስ አበባ፤ ግንቦት 19/2017(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በጣሊያን ሮም ያደረጉት ቆይታ ስኬታማ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው በጣሊያን ሮም ያደረጉትን ቆይታ አስመልክቶ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ልዑካን ቡድናቸው ስኬታማ ቆይታ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በቆይታቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ሊዮ 14ኛ ጋር በቫቲካን ሰፋ ያለ ውይይታ ማድረጋችውን ጠቅሰዋል።
በውይይቱ ኢትዮጵያ እና ቫቲካን በትምህርት ልማት፣ በዓለም ሰላም እና በባለብዙ ዘርፍ እና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ወዳጅነት አጠናክረው ለመቀጠል ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ቫቲካን በትምህርት ልማት ላይ እያደረገች ያለውን ድጋፍ ለማጠናከር መግባባት ላይ መደረሱንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂኦርጂያ ሜሎኒ ጋር ሰፋ ያለ የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።
በውይይታቸው ባለፉት ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወዳጅነት ወደ ላቀ ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑንም አብራርተዋል።
ጣሊያን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገትና ሪፎርም እንዲሁም ለኢነርጂ ዘርፍ ልማት ድጋፍ እያደረገች መሆኗ በውይይቱ ወቅት መነሳቱን ጠቁመዋል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ጣሊያን በኢትዮጵያ እያደረገች ያለው የልማት ፋይናንስ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በቆይታቸው በአረንጓዴ ልማት፣ በከተማና ሌሎች ልማቶች የሚደግፉ ስምምነቶች መደረጋቸውን የገንዘብ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ጠቅሰዋል።
ይሄም በኢትዮጵያ እና በጣሊያን መካከል ያለው የልማት ፋይናንስ ትብብር እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ተጠናክሮ እንዲቀጥል የጣሊያን መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግ ከስምምነት መደረሱንም ተናግረዋል።
የጣሊያን ባለሃብቶች ሪፎርሙ የፈጠረውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዲጠቀሙ ሀሳብ መቅረቡን አመልክተው፤ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ በመሳተፍ በትብብር አብሮ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣሊያን ቆይታቸው በባለብዙ እና በሁለትዮሽ ጉዳዮች ሰፋ ያለ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተው፤ የጣሊያን መንግስት ለኢትዮጵያ የሚሰጠው የልማት ፋይናንስ፣ የሪፎርም እና የኢነርጂ ዘርፎች ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከስምምነት መደረሱን ተናግረዋል።
የሮም ቆይታቸው የተጀመረውን ሪፎርም አጠናክሮ ለመቀጠል የጣሊያን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ማረጋገጥ ያስቻለ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መካከል ያለው ጠንካራ ግንኙነት ለሀገራቱ ወዳጅነት መጠናከር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑንም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ከዊቢዩልድ ግሩፕ(Webuild Group) ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፔይትሮ ሳሊኒ ጋር የተደረገው ውይይት ስኬታማ እንደነበር አንስተዋል።
በውይይቱ ኩባንያው በኢትዮጵያ የያዛቸው ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲያጠናቅቅ ሀሳብ መነሳቱን አመልክተዋል።
እንዲሁም ኩባንያው በቤት፣ በኢነርጂ፣ በማዕድን ልማትና በማዳበሪያ ዘርፍ ላይ በስፋት እንዲሳተፍ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መጋበዛቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ በትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ባቀረቡት ግብዣ መሰረት አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን መናገራቸውን ጠቁመዋል።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025