አርባ ምንጭ፤ ግንቦት 27/2017(ኢዜአ)፦ የመንግስትና የህዝብ ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የምክር ቤት አባላት የሚያከናውኑትን የቁጥጥርና የክትትል ሥራ ማጠናከር እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ሎሚ በዶ ገለጹ።
ምክትል አፈ-ጉባኤዋ ይህን ያሉት በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ባለው 23ኛው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የዋና ኦዲተሮች እና ባለድርሻ አካላት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ነው።
በየደረጃው ባሉ የመንግስት ተቋማት ብልሹ አሠራር፣ ህገ-ወጥ ተግባር እና ስልጣንና ሃላፊነትን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ እንደሚስተዋል ጠቅሰው፣ ይህም በሀገራዊ አድገት ላይ ጫና እያሳደረ ይገኛል ብለዋል።
በየደረጃው ያሉ የምክር ቤት አባላትና አፈ ጉባኤዎች በጀት ከማጽደቅ ባለፈ የህዝብና የመንግስት ውስን ሀብት ለታለመለት ዓላማ እንዲውል የሚያከናውኑትን የክትትልና የቁጥጥር ሥራ ማጠናከር እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ከፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ጋር በቅርበት በመስራት የኦዲት ግኝቶችን ከመፈተሽ ባለፈ በአጥፊዎች ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
የመንግስት ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶችን ከብልሹ አሠራር ለማጽዳት የኦዲት ተቋማት ሚና ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ከተቋማዊ ሥራ ባሻገር ለሀገራዊ የኦዲት አሠራር ውጤታማነት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
ህገወጥነትና ብልሹ አሠራሮችን ከማጋለጥ ባለፈ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ምክትል አፈ ጉባኤዋ ጠቁመዋል።
የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው በየደረጃው ከሚገኙ የህዝብ ተወካዮች ጋር በመቀናጀት የሀገርና የህዝብ ውስን ሀብትን ከምዝበራ ለመታደግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
ተቋማቸው በክልሎችና በከተሞች አስተዳደር ካሉ ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች ጋር ጠንካራ ተዋረዳዊ የሥራ ግንኙነት እንዳለውም ጠቅሰዋል።
የሀገሪቱን የኦዲት ሥራ ይበልጥ ከፍ ለማድረግ ለኦዲተሮች በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ መሠረት አቅም የመገንባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በመንግስት ከሚሰሩ ሥራዎች በተጨማሪ ህዝብም ክፍተቶችን ሲያይ ፈጥኖ ጥቆማ በመስጠት የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ለሦስት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ የፌደራል፣ የክልል እና የከተሞች ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች፣ የቋሚ ኮሚቴዎች አባላትና ዋና ኦዲተሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
አሶሳ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልዱ አሻራና ኩራት ነው ሲሉ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አብዱልሙህሲን ሐሰን...
Feb 28, 2025
ሚዛን አማን፤የካቲት 20/2017 (ኢዜአ)፦በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ በማህበር ተደራጅተው በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ በመ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤የካቲት 4 /2017(ኢዜአ)፦ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በግብርናው ዘርፍ እያከናወነ ያለው በምርምር የተደገፈ ስራ ምሳሌ የሚሆን ነው ሲሉ የሕዝብ ተወካዮች ም...
Feb 12, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 1/2017(ኢዜአ)፡- የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል መገንባት በክልሉ ለግብርና ስራው መሠረታዊ የሆነ...
Feb 8, 2025