🔇Unmute
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ ገለጹ።
የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር (EFFSAA)፣ ከተለያዩ የመንግሥት፣ የግል እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ የሎጂስቲክስ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ዕውቅና ባለው የፊያታ (FIATA) ዲፕሎማ አሰልጥኖ አስመርቋል፡፡

በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ ዴንጌ ቦሩ እንደገለጹት፤ መንግሥት ለዘርፉ ሪፎርም ልዩ ትኩረት በመስጠት ስትራቴጂ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
ሎጂስቲክስ ዕቃዎችን ማጓጓዝ ብቻ ሳይሆን የሀገር ኢኮኖሚ ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር የሚያገናኝ መረብ ነው ብለዋል።
መንግሥት የወጪና የገቢ ምርቶችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጥራት ለማሳለጥ የሎጂስቲክስ ዘርፉን በሰለጠነ የሰው ኃይል ለማጠናከርና ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና በዲጂታል ኢኮኖሚ የተጀመሩ የብልጽግና ጉዞዎች ውጤታማ መሆን የሚችሉት አስተማማኝ የሎጂስቲክስ ሥርዓት ሲኖር ብቻ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሎጂስቲክስ ዘርፍ ካልዘመነ በስተቀር ምርቶችን በጥራት፣ በሰዓቱና በቅናሽ ዋጋ ለገበያ ማቅረብ እንደማይቻልና የሀገር ውስጥ ምርቶችም በዓለም መድረክ ተወዳዳሪ መሆን እንደማይችሉ አስረድተዋል።

ዛሬ የተመረቁት የፊያታ ዲፕሎማ ባለሙያዎች የሀገሪቱን የአቅርቦት ሰንሰለት በማዘመን ረገድ ትልቅ አደራና ኃላፊነት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ሰልጣኞችና የዘርፉ ተዋናዮች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችና ባለሀብቶች ወደ ሀገር ውስጥ በሚመጡበት ወቅት የሚፈጠሩትን ዕድሎች ለመጠቀም ከአሁኑ ዝግጁ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የሎጂስቲክስ ሥርዓትን ማዘመንና ወቅቱን የዋጀ አሠራር መዘርጋት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ አጠቃላይ የዘርፉን ትራንስፎርሜሽን ለማሳለጥ የሚያስችል የአሥር ዓመት ስትራቴጂ ተቀርጾ ወደ ተግባር መግባቱን ይፋ አድርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተግዳሮቶችና የኢትዮጵያ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ የሚፈጥሩትን ተጽዕኖ ለመቋቋም የራስን ሥርዓት በራስ አቅም መገንባት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የውጭ ኢንቨስትመንት ዕድልን በአግባቡ ለመጠቀምና የሀገሪቱን የንግድ ተወዳዳሪነት ለማረጋገጥ በሳይንሳዊና በዘመናዊ ዕውቀት የሰለጠኑ ባለሙያዎች ሚና የማይተካ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ የዕቃ አስተላላፊዎች እና የመርከብ ወኪሎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ዳዊት ውብሸት (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይህ የፊያታ ዓለም አቀፍ ሥልጠና በኢትዮጵያ ያለውን የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ትልቅ እምርታ መሆኑን ገልጸዋል።

ማኅበሩ አቅምን በመገንባትና የገበያ ትስስርን በመፍጠር ረገድ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ሰልጣኞች በበኩላቸው፤ የወሰዱት ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና የሙያ ብቃታቸውን ከማሳደግ ባለፈ ሀገራቸውን በላቀ ደረጃ ለማገልገል ትልቅ መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል።

ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ በስልጠናው የተሳተፉት አቶ አምባዬ ገብርኤል፤ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስልጠና መውሰዳቸው የስራ ብቃታቸውን ለማሳደግ ከፍተኛ እገዛ አለው ብለዋል።
የተሻለ ሥራ ለመሥራትና ሀገራቸውን በላቀ ሁኔታ ለማገልገል ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከፔቭ ሎጂስቲክስ የመጡትና የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት አቶ ይርጋለም አዲስ በበኩላቸው፣ ስልጠናው ትልቅ እውቀትና ክህሎት እንዳስጨበጣቸው ገልጸዋል።
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 7/2018 (ኢዜአ)፦ መንግሥት የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ ዘርፍ በማዘመን የገቢና የወጪ ንግድን ቀልጣፋ በማድረግ የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለማ...
Jul 16, 2026
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 27/2018 (ኢዜአ)፦የሀዋሳ ከተማን የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስ...
Jul 7, 2026
ኮምቦልቻ፤ ሰኔ 23/2018 (ኢዜአ)፡- የአዋሽ-ኮምቦልቻ- ሃራ ገበያ ባቡር መስመር ፕሮጀክት ጥገናን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ...
Jul 1, 2026
አዲስ አበባ፤ሰኔ 22/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ጣሊያን የ70 ሚሊዮን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ በረጅም ጊዜ የሚከፈል የብድር ስምምነ...
Jun 30, 2026