
ዲላ፤ግንቦት 24/2017 (ኢዜአ)፦በምዕራብ ጉጂ ዞን የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች የቡና ልማት ምርታማነትን በእጥፍ ማሳደጋቸውን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አመለከተ።
በዞኑ የሚገኘው ቀርጫንሼ ግሩፕ ዘመናዊ የቡና እርሻ ከሶስት ሚሊዮን በላይ የተሻሻሉ የቡና ችግኞችን ለአርሶ አደሮች ማሰራጨት ጀምሯል።
የቡና ስርጭቱም በዞኑ አምስት ወረዳዎች ከሶስት ሺህ የሚልቁ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቱኬ አና በወቅቱ ለኢዜአ እንዳሉት፥በዞኑ የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ለተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች ልማት ትኩረት ተሰጥቷል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት ያረጀና በበሽታ የተጠቃ ቡናን በማንሳት በተሻሻሉ ዝርያዎች ለመተካት በተደረገ ጥረት ሰባት ኩንታል በሄክታር የነበረውን የዞኑን አማካይ ምርታማነት ከእጥፍ በላይ በማሳደግ 15 ኩንታል ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
በዚህም በዞኑ የቡና ልማት ሽፋኑን ከ141 ሺህ ሄክታር በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል።
ዞኑ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ከ101 ሺህ ቶን በላይ ጥራቱን የጠበቀ ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉንም ገልጸዋል።
ቀርጫንሼ ግሩፕ ዘመናዊ የቡና እርሻ ዘመናዊ አሰራርን ለዞኑ አርሶ አደሮች ከማስተዋወቅ ባለፈ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በማሰራጨት ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ እንደሚገኝም ሃላፊው ተናግረዋል።
ቀርጫንሼ ግሩፕ ዘመናዊ የቡና እርሻ በጠብታ መስኖ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና በመሸፈን በሄክታር ከ40 ኩንታል በላይ ምርት እያገኘ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በድርጅቱ የሰርተፊኬሽንና ዘላቂ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱ ኢታና ናቸው።
ምርቱን በጥራት አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ በማቅረብም ከራሱ አልፎ ሀገርን እየደገፈ መሆኑን አንስተው፥ ተሞክሮውን ለማስፋት በስሩ ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማቀፍ የተቀናጀ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ነው ያነሱት።
ዛሬ የመጀመሪያ ምዕራፍ ተጠቃሚ ለሆኑ ከሶስት ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ከሶስት ሚሊዮን የሚልቁ የተሻሻሉ የቡና ችግኞች ስርጭት መደረጉን ጠቅሰው፥ መሰል ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በዞኑ የቡሌ ሆራ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ተሰማ ሮባ በበኩላቸው፥ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከአራት ሄክታር በላይ ማሳቸውን በተሻሻሉ የቡና ዝርያዎች መቀየራቸውን ተከትሎ ምርታማነታቸውን በእጥፍ ማሳደጋቸውን አንስተዋል።
በተያዘው ዓመትም ከ1 ሺህ 500 በላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል።
ከቀርጫንሼ ግሩፕ ያገኙትን የችግኝና የክህሎት ድጋፍ ከልምዳቸው ጋር በማቀናጀት ችግኞችን በመትከልና በመንከባከብ ምርታማነትን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አርሶ አደር አብዱልቃድር ጉያ በበኩላቸው፥ ቡናን በባህላዊ መንገድ ማልማት ምርታማነት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ከቀርጫንሼ ግሩፕ ዘመናዊ የእርሻ ልማት ተሞክሮ በመውሰድ የተሻሻሉ ዝርያዎችን በዘመናዊ መንገድ እያለሙ መሆናቸውን አንስተዋል።
ዛሬ ከ400 በላይ የተሻሻሉ ዝርያዎችን መረከባቸውን ጠቅሰው፥ በቀጣይ የተሻለ ምርት ለማግኘት ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የቀርጫንሼ ግሩፕ ዘመናዊ የቡና እርሻ ልማት ከጥላ ዛፍ ውጪ በቴክኖሎጂ በተደገፈ ቡናን በጠብታ መስኖ የማልማት አዲስ አሰራረን ያስተዋወቀ ድርጅት ሲሆን ከዚህ ቀደምም በጠቅላይ ሚኒስትሩና በሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ምልከታ እንደተከናወነለት ይታወሳል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026