አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2017(ኢዜአ)፦ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን ቀልጣፋና ተወዳዳሪ ለማድረግ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሎጂስቲክስ ዘርፍ ከተሰማሩ ድርጅቶች ጋር ውይይት አካሂደዋል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በመድረኩ፤ የሀገርን የብልፅግና ጉዞ ለማፋጠን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎትን ቀልጣፋ ማድረግ የግድ ነው ብለዋል።
ዘርፉን ተወዳዳሪና ደህንነቱ የተጠበቀ ለማድረግ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አፅንኦት ሰጥተዋል።
የመርከብ አገልግሎት አሰጣጥን ከደንበኞች ፍላጎት ጋር ማጣጣምና የተጋነነ ዋጋ ካለ መፈተሽ ያስፈልጋል ነው ያሉት።
በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት አገልግሎታቸውን ለማሻሻል የሪፎርም ስራዎች እያከናወኑ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በዘርፉ ለብልሹ አሰራር የተጋለጡ ስራዎችን መፈተሽና ከሰው ንክኪ ነጻ የሆነ አሰራርን መተግበር እንደሚገባም ተናግረዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የሎጂስቲክስ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በበኩላቸው፥ ከመርከብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ከጭነት ሚዛን ቁጥጥር፣ ከዋጋ ተወዳዳሪነትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን አንስተዋል።
የዕቃ ማጓጓዣ ኮንቴነሮች እጥረት እንዲፈታና የመርከብ አገልግሎት ለማግኘት ፈጣን ምላሸ እየተሰጣቸው ባለመሆኑ እንዲስተካከል ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ(ዶ/ር)፥ አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኘው በተቋሙ አሥር መርከቦችና ተጨማሪ መርከቦችን ደግሞ በመከራየት መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በኪራይ የሚቀርቡ መርከቦችን ወደ አገልግሎት ለማሰማራት ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አንዱ ችግር ነው ብለዋል።
የዘርፉን አገልግሎት ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ መመሪያዎችን የማሻሻል ስራ እየተሰራ ነው ያሉት ዶክተር በሪሶ፥ በኦንላይን የተደገፈ አሰራር ሙሉ ለሙሉ በቅርቡ እንደሚጀመር ነው የገለጹት።
የመርከቦችን ቁጥር ለመጨመር የግዢ ሂደት ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍራኦል ጣፋ፥ አገልግሎት የሚሰጥባቸውን የመዳረሻ ሀገራት ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ሀብታሙ ሀይለሚካኤል በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስን የአገልግሎት አቅምና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ለማጎልበት እንዲሁም፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እንሰራለን ብለዋል።
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ የስንዴ ልማት ስራዎችን ለማስፋት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 20/2017(ኢዜአ)፦ባለፉት ስድስት ዓመታት የፋይናንስ ዘርፉንና የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል አሰራር በመቀየር የግዥ ስርዓቱን ዓ...
Feb 28, 2025
አዲስ አበባ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናውን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፕሮጀክት መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳን...
Feb 24, 2025
ጋምቤላ፤ የካቲት 15/2017(ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል በቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የዜጎችን ተጠቃሚነት እውን ያደረጉ የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተገንብ...
Feb 24, 2025