
ዲላ፤ሰኔ 19/2017 (ኢዜአ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማፍለቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ በምርምር ሥራዎች ላይ ያተኮረ የመጀመሪያው ዓመታዊ አውደ ጥናት በዲላ ከተማ ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከ159 በላይ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ቀርበው የመጨረሻ ግምገማ መካሄዱም ተመላክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ያሲን ጎአ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በምርምር በማፍለቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው።

በተለይ በሰብል፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በእንስሳት ልማት የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ የማስተዋወቅና የማስፋት ሥራ ትኩረት ሰጥቶ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም የግብርና ምርታማነትንና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ መቻሉን ነው የገለጹት።
በአውደ ጥናቱ ከ159 በላይ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ለመጨረሻ ግምገማ መቅረባቸውንና የተመረጡትንም ለአርሶ አደሩ የማሸጋገር ሥራ እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ኢንስቲትዩቱ በእንሰትና ሥራስር ሰብሎች የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ በማስተላለፍ ምርታማነትን ማሳደጉን የገለጹት ደግሞ የአረካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ገነነ ገዛኸኝ ናቸው።

በተለይ በሽታን ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ የቆላ የእንሰት ዝርያን በማስተዋወቅ በክልሉ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን አመልክተዋል።
በሙከራ ላይ የሚገኙ የእንሰት ማቀነባበሪያና መፋቂያ ቴክኖሎጂዎችን ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ለእዚህም የአውደ ጥናቱ እገዛ የጎላ ነው ብለዋል።
የጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተክሌ ዮሴፍ በበኩላቸው፤ በማዕከሉ ለአርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለማቅረብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያዘው ዓመት ተፈትሸው የወጡ የበቆሎ፣ ቦሎቄና ማሽላ ዝርያዎችን በማባዛትና በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰሩ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
በተለይ ለተለያዩ ሥነ-ምህዳሮች ምቹ የሆኑ የሰብል ዝርያዎችን ከማስተዋወቅ ባለፈ ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ከእንስሳት ልማት ጋር የተያያዙ ስራዎችን በመስራት አርብቶ አደሩን በቅርበት እያገዙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በአውደ ጥናቱ ላይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ከምርምር ማዕከላት የመጡ የተለያዩ ምሁራን ተገኝተዋል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026