🔇Unmute
ሚዛን አማን፤ጥቅምት 22/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል አዲሱን የተሽከርካሪ ሰሌዳ ለማሰራጨት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል እና የትራንስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዘመዴ አንዳርጌ ለኢዜአ እንደገለጹት አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በቴክኖሎጂ የተደገፈና የተለያዩ መረጃዎችን አካቶ የተዘጋጀ ነው።
ይህም ነባሩ ሰሌዳ ለሕገወጥ ተግባር ያለውን ተጋላጭነት ከማስቀረት ባለፈ ክልላዊ መለያ ያለውን ታርጋ ስለሚያስቀር ለሀገራዊ አንድነት መጠናከር አስተዋጾ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
የተሽከርካሪ መረጃዎችን በዲጂታል አሰራር ለመለየት የሚያስችልና ከዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ተዛማጅ እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ በመሆኑ ለአሠራርና ለቁጥጥር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር አክለዋል።
አዲሱን ሰሌዳ በክልሉ ውስጥ ላሉ ከ34 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ለማሰራጨት አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አቶ ዘመዴ ተናግረዋል።
እስካሁንም አስፈላጊ መረጃዎችን ለይቶ ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የማሳወቅና መሰል ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቁመው፣ ለዚሁ ተግባር 20 ሚሊዮን ብር በጀት መመደቡንም አመልክተዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡ አሽከርካሪዎች መካከል አቶ ሺመልስ ታደሰ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ እንደሀገር ወጥ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱ በነጻነት ተንቀሳቅሶ ለመስራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተናግሯል።
"ከክልል ወደ ክልል ተዘዋውሮ ለመሥራት በሚደረግ እንቅስቃሴ በተለያዩ ምክንያቶች ሲገጥመን የነበረን እንግልት ያስቀራል" ሲልም ተስፋውን ገልጿል።
ሰሌዳው እንደሀገር ወጥ በሆነ መንገድ መዘጋጀቱ የብዙዎች ፍላጎት እንደነበር አስታውሶ ይህም ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከርና በሁሉም ክልሎች በነጻነት ለመንቀሳቀስ ያግዛል ብሏል።
በትራፊክ አሰራር ላይ ሲስተዋል የነበረውን ብልሹ አሠራር ያስቀራል የሚል እምነት እንዳለው የተናገረው ደግሞ ሌላው አሽከርካሪ አዝማች አደመ ነው።
መንግስት የተሽከርካሪ ሰሌዳን ሀገራዊ አድርጎ በአዲስ መልክ የማዘጋጀቱ ጥረት የሚበረታታና የሚደገፍ መሆኑን ተናግሯል።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው በሀገር አቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ ያለውን ሰሌዳ በተያዘው ዓመት ሙሉ በሙሉ በአዲስ የመተካት ሥራ ይከናወናል።
ነባሩ ሰሌዳ ከዘርፉ እድገትና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ በአዲስ ሰሌዳ መተካት ማስፈለጉም ቀደምሲል መገለጹ የሚታወስ ነው።
አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር የሚመራ በመሆኑ ለቁጥጥር ስርዓትም አመቺ እንደሆነም ተመላክቷል።
ሰሌዳው ስለተሽከርካሪው ሙሉ መረጃ የሚሰጡና ተቆጣጣሪ አካላት በቴክኖሎጂ የሚለዩዋቸው ሚስጥራዊ መረጃዎችን ያካተተ እንደሆነም የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።
በታዋቂው ታይም መጽሔት (TIME Magazine) ላይ እንግሊዛዊው ጸሐፊ ጆሽ ዊልሰን “THE POWER TO UNITE AFRICA” (አፍሪካን የማስተሳሰር ኃይል)...
Sep 14, 2026
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮ...
Sep 7, 2026
ጅማ ነሐሴ 27/2018 (ኢዜአ):- ከዝናብ ጥገኝነት በመላቀቅ ወደ መስኖ ልማትና ሜካናይዜሽን እየተደረገ ያለው ሽግግር፣ በኢትዮጵያ ግብርና ውስጥ አዲስ ምዕራፍ...
Sep 3, 2026
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 21/2018(ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጥጥ ልማትን በጥራትና በብዛት በማምረት ለጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት ለማቅረብ ልዩ ትኩረት ...
Aug 28, 2026